ኢሳት (መስከረም 4 ፥ 2008)
የአሜሪካን ምክር ቤት አባላት ሃገሪቱ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጠንካራ እርምጃን እንድትወስድ በማስተዋወቅ ላይ ያሉት የውሳኔ ሃሳብ በበርካታ አለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ ድጋፍ በማግኘት ላይ መሆኑን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገለጸ።
ይኸው በአሜሪካ የምክር ቤት አባላት ዘንድ እየተዋወቀ የሚገኘው የውሳኔ ሃሳብ የአሜሪካን መንግስት በኢትዮጵያ መንግስት የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማውገዝ ለሃገሪቱ በሚሰጡ የተለያዩ ድጋፎች ላይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ ይጠይቃል።
ክሪስ ስሚዝ፣ ኬይት ኤሊሰን እና ማይክ ኮፍማን የተባሉ የምክር ቤት አባላት በኢትዮጵያ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ግድያዎች በሃገራቸው መንግስት በኩል ልዩ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ ዘመቻን እያካሄዱ እንደሆነ ታውቋል።
የምክር ቤቱ አባላት እያካሄዱ ያሉትን ዘመቻ በመደገፍ ከ10 የሚበልጡ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ሂውማን ራይትስ ዎች በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ፍሪደም ሃውስ፣ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ፕሮጄክት፣ ሂውማን ራይስት ዎች፣ ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ሰብዓዊ መብቶች፣ ኦሮሞ አድቦኬሲ አሊያንስ፣ እንዲሁም የአለም አቀፍ የስቃይ ሰለባዎች ድጋፍ ጥምረት ድጋፋቸውን ከሰጡት ተቋማት መካከል መሆናቸው ታውቋል።
በአሜሪካ የምክር ቤት አባላት ዘንድ እየተዋወቀ የሚገኘው የውሳኔ ሃሳብ በቅርቡ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎችን እንዲሁም የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአለም አቀፍ ገለልተኛ ቡድን ምርመራ እንዲካሄድበት ይጠይቃል።
የውሳኔ ሃሳቡ በሌሎች የምክር ቤት አባላትና ድርጅቶች በኩል ድጋፍን እያገኘ እንደሆነ የተናገሩት ክሪስ ስሚዝ፣ የውሳኔ ሃሳቡ ተፈጻሚ እስኪሆን ድረስ ዘመቻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ማክሰኞ ከአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ግምት ውስጥ በማስገባት የአሜሪካ መንግስት ለሃገሪቱ በሚሰጠው የደህንነት ጸጥታ ድጋፍ ላይ እርምጃ እንዲወስድ የውሳኔ ሃሳቡ የሚጠይቅ ሲሆን፣ አለም አቀፍ የልማት አጋሮችም ተመሳሳይ አቋምን እንዲይዙ ያሳስባል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሌሎች የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት ለውሳኔ ሃሳቡ ድጋፋቸውን በመስጠት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አክሎ ጠይቋል።
በሃገሪቱ የተፈጸሙ ግድያዎችን እና የጅምላ እስራትን ተከትሎ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ከመጠን ያለፈ የሃይል እርምጃ መፈጸሙን መግለጹ ይታወሳል። በዚሁ የመንግስት የሃይል እርምጃ ከ500 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።
በተለያዩ አካባቢዎች ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ ዕልባት ባለማግኘቱ ምክንያት የየክልል ባለስልጣናት ከነዋሪዎች ጋር በመምከር ላይ እንደሚገኙም ከሃገር በኢት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ይኸው ለወራት የዘለቀው ተቃውሞ በመንግስት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ስርዓት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።