ኢሳት (መጋቢት 29 ፥ 2009)
የሶሪያ መንግስት ከቀናት በፊት በንጹሃን የሃገሪቱ ዜጎች ላይ ፈጽሞታል የተባለውን የኬሚካል የጦር መሳሪያ ዕርምጃ ተከትሎ አሜሪካ በተመረጡ የሃገሪቱ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ የሚሳይል ጥቃት መውሰዷን ሃሙስ ይፋ አደረገች።
የአሜሪካ ወታደራዊ ባለስልጣናት ከምስራቅ የሜዲትራኒያን ባህር ላይ ከወታደራዊ መርከቦች የተወሰደው የሚሳይል ጥቃት በቅርቡ በሰሜናዊ ምዕራብ የሶሪያ ግዛት ጥቃት ለመፈጸም አገልግሎት የሰጠ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ዋነኛ ኢላማ እንደነበር ገልጸዋል።
የአሜሪካ የባህር ሃይል አባላት 59 ቶምሃውክ የተሰኘ የረቀቀ የሚሳይል ጥቃት በምዕራብ የሆምስ ግዛት በማስወንጨፍ የሶሪያ መንግስት ወታደራዊ ይዞታዎች እንዳወደሙ ቢቢሲ ዘግቧል።
የሶሪያ ባለስልጣናት በበኩላቸው በጥቃቱ በትንሹ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን በመግለፅ እርምጃው የአለም አቀፍ ህግን የጣሰ ድርጊት እንደሆነ አስታውቀዋል።
የሶሪያ ወዳጅ የሆነችው ሩሲያ የአሜሪካንን ወታደራዊ ጥቃት አጥብቃ የኮነነች ሲሆን፣ ከአሜሪካ ጋር በሶሪያ በኩል ግጭት እንዳይፈጠር የተደረሰን ስምምነት ለጊዜው እንዳቋረጠች ይፋ አድጋለች። የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የሃገራቸው መከላከያ ሚኒስቴር ሶሪያ በተመሳሳይ የኬሚካል የጦር መሳሪዎችን እንዳትጠቀም የሚያስችል ወታደራዊ ዘመቻ እንዲወስን ትዕዛዝ መስጠታቸውን ገልጸዋል።
ብሪታኒያና የተለያዩ የምዕራብ ሃገራት አሜሪካ የወሰደችው ጥቃት ተገቢ ምላሽ እንደሆነ ምላሽን ሰጥተዋል።
ሃሙስ የተፈጸመው ጥቃት ቀጣይ ይሁን አይሁን የአሜሪካ ወታደራዊ ባለስልጣናት የሰጡት ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ምክር ቤት አርብ በጉዳዩ ዙሪያ አስቸኳይ ስብሰባ ያካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።