(ኢሳት ዲሲ–ጥር 13/2011)የአሜሪካ መንግስት በሶማሊያ በአልሻባብ ይዞታዎች ላይ የሚያደርሰውን የአየር ጥቃት አጠናክሮ መቀጠሉ ታወቀ።
በሳምንቱ መጨረሻ በአልሻባብ ላይ በተሰነዘረ የአየር ጥቃት 52 ታጣቂዎች ተገድለዋል።
አሜሪካ ባሳለፍነው የምዕራባውያኑ ዓመት 2018 ብቻ 47 የአየር ጥቃት ማድረሷም ተመልክቷል።
አልሻባብ ባለፈው ሳምንት በኬንያ ናይሮቢ በዘመናዊ ሆቴል ላይ እንዲሁም በመቋደሾ በወታደሮች ካምፕ ላይ በተሰነዘረው ጥቃት በአጠቃላይ 30 ያህል ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።
ይህ የሶማሊያ ጽንፈኛ ሃይል በመኪና ሲጓጓዙ በነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይም በተመሳሳይ ጥቃት በማድረስ ቁጥራቸው ያልታወቁ ወታደሮች መሞታቸው ተመልክቷል።
አልጀዚራ እንደዘገበው አልሻባብ በሞቃድሽ በሶማሊያ ወታደሮች ካምፕ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ 8 ወታደሮችን ገድሏል።
አልሽባብ የገደልኩት 15 ነው ሲል መግለጫ ሰቷል።
አሜሪካ ለአልሽባብ የሰሞኑ እንቅስቃሴ በሰጠችው የአየር ጥቃት አጸፋ ባለፈው ቅዳሜ 52 የአልሻባብ ታጣቂዎች ተገድለዋል።
የአሜሪካ የአፍሪካ ዕዝ እንዳስታወቀው የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው የሶማሊያ ማዕከላዊ ጁባ ግዛት ጂሊብ በተባለ ቦታ ሲሆን 52 የአልሻባብ ወታደሮች ተገድለዋል።
የጁባ ላንድ አስተዳደር የጸጥታ ሃላፊ አብዲልረሺድ ሐሰን አብዲኑር ለመንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ በአልሻባብ ላይ በተሰነዘረው ጥቃት የሞቱት የአልሻባብ ታጣቂዎች ቁጥር 73 እንደሆነም ገልጸዋል።
አሜሪካ በሶማሊያ የአልሻባብ ይዞታዎች ላይ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2017 ጀምሮ እንደገና የአየር ጥቃት የቀጠለች ሲሆን ይህም ከግዜ ወደግዜ እየተጠናከረ መሄዱ ተመልክቷል።
ባለፈው ዓመት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 ብቻ 47 የአየር ጥቃት በአልሻባብ ይዞታ ላይ መፈጸሟም ይፋ ሆኗል።
ኢትዮጵያ 66 የአልሻባብ ታጣቂዎችን መግደሏን አስታውቃለች።
በሶማሊያ ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀሰው አልሻባብ ደቡባዊን የሃገሪቱን ገጠራማ ክፍል እና ማዕከላዊውን ክፍል ይቆጣጠራል።