ኢሳት (ግንቦት 1 ፥ 2009)
አሜሪካ ለኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የምትሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ለሙስና የተጋለጠ ነው በማለት ድጋፏን አቋረጠች። የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴት ለኬንያ መንግስት ባሳወቀው በዚሁ ውሳኔ 12 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ድጋፍ እንዲቋረጥ መደረጉን እንደገለጸ ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ማክሰኞ ዘግቧል።
በኬንያ የአሜሪካ አምባሳደር ሮበርት ጎዴክ በሃገሪቱ ሙስናና ተጠያቂነት አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ለኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በቀጥታ የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ እንዲቋረጥ መደረጉን ለዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ አስረድተዋል።
አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለተለያዩ ሃገራት ስትሰጥ በቆየችው የልማት ድጋፍ ላይ ቅነሳን እንደምታደርግ ካሳወቀች በኋላ በኬንያ መንግስት ላይ የተወሰደው ዕርምጃ የመጀመሪያን መሆኑ ታውቋል።
አምባሳደር ሮበርት ለኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚሰጠው ድጋፍ ለታለመለት አላማ መዋሉ ጥያቄን በማስነሳቱ ውሳኔው ሊወሰድ መቻሉን አብራርተዋል። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለደሞዝ ክፍያ፣ ስብሰባዎች፣ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የሚያወጣው ወጪ በእገዳው ምክንያት መስተጓጎሉን ቢቢሲ ዘግቧል።
አሜሪካ የ12 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ የሚጠጋ ገንዘቡን ማቋረጧ በሁለቱ ሃገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ መሻከርን ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ቢሰጋም የአሜሪካው አምባሳደር ሮበርት ጉዴክ እንዲቋረጥ የተደረገው ድጋፍ ሌላ ተልዕኮ እንደሌለው ምላሽን ሰጠዋል።
ሃገራቸው ለጊዜው የያዘችው የገንዘብ ልገሳም በቀጥታ ለኬንያዊያን አገልግሎት በማይውለው ላይ መሆኑን አምባሳደሩ አክለው አስረድተዋል። ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ መንግስት ለኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳና ሌሎች ሃገራት በቀጥታ በሚሰጣቸው የልማት ድጋፍ ላይ ቅነሳ እንዲደረግ መወሰኑ ይታወሳል።
ሃገሪቱ በወሰደችው በዚሁ ዕርምጃ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ በምታገኘው የልማት ድጋፍ ላይ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ በማጣት ተጎጂ ሃገር ከሆኑት መካከል ዋነኛዋ ሆናለች።
የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ለታዳጊ ሃገራት ሲሰጥ የቆየው የልማት ድጋፍ እንዲቀንስ ከማድረጉ በተጨማሪ ልገሳው አደ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማበረታቻ እንዲለወጥ ማደረጉንም ለመረዳት ተችሏል። አዲሱ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከገንዘብ ልገሳው በተጨማሪም በውጭ ፖሊሲው ላይ አዳዲስ ማሻሻያዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ተመልክቷል።