አሜሪካውያን ወደኢትዮጵያ እንዳይጓዙ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማሳሰቢያ አወጣ

ኢሳት (ኅዳር 28 ፥ 2009)

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሃገሪቱ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ በድጋሚ ማሳሰቢያን አወጣ።

ባለፈው አመት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ፖለቲካዊ ውጥረትና አለመረጋጋት ማስፈኑን ያስታወቀው የአሜሪካ መንግስት፣ አሜሪካዊያን ችግሩ ዕልባት ወደአላገኘባት ኢትዮጵያ ቢጓዙ የደህንነት ስጋት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል አሳስቧል።

ዜጎቹ ወደ ሃገሪቱ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ ያሳሰበው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ተጥሎ ያለው እገዳ ለዜጎቹ የተሟላ መረጃን ለማድረስ እንዳላስቻለው አስታውቋል።

ችግሩ ዕልባት ባላገኘበት ወቅት አሜሪካዊያን ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ የጠየቀው የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተጓዦች ቢኖሩ እነዚህን ችግሮች ግምት ውስጥ ማስገባት እንዳለባቸው አሳስቧል።

ከአንድ ወር በፊት አሜሪካ ዜጎቿ ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ ተመሳሳይ መልዕክትን አስተላልፋ የነበረ ሲሆን፣ ይኸው ማሳሰቢያ ቀጣይ እንዲሆን መወሰኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዜጎቹ ባሰራጨው የማሳሰቢያ መልዕክት አስፍሯል።

የጉዞ ማሳሰቢያው ከወጣ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙና የመሄድ ዕቅድ ያላቸው አሜሪካዊያን ወደ ሃገሪቱ ከገቡ በኋላ አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ተመዝግበው መረጃዎችን እንዲከታተሉ በመግለጫው ተመልክቷል።

አሜሪካ ዜጎቿ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ በመጀመሪያ ዙር ያወጣቸውን ማሳሰቢያ ተከትሎ የመንግስት ባለስልጣናት ዕርምጃው ወቅታዊ አይደለም በማለት ቅሬታ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ይሁንና የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይን በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነ የሚገልጸው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማሳሰቢያውን ዳግም ማውጣት እንዳስፈለገ አክሎ አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በቅርቡ በአማራ ክልል ራሳቸውን ባደራጁ የነጻነት ሃይሎችና በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መካከል የተቀሰቀሰን ግጭት ተከትሎ በአካባቢው የጉዞ ማሳሰቢያን አውጥቶ የነበረው የብሪታኒያ መንግስት ዜጎች አሁንም ድረስ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

የብሪታኒያ ዜጎች እጅግ አስፈላጊ ካልሆነ ስራ በስተቀር በክልሉ ስር ከሚገኙ የጸገዴ፣ የምዕራብ አርማጭሆ እና የታች አርማጭሆ እንዲሁም የሰሜን ጎንደር ስፍራዎች ከመጓዝ እንዲቆጠቡ የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድጋሚ አሳስቧል።

የብሪታኒያ መንግስት ባለፈው ወር ያሰራጨውን የጉዞ ማሳሰቢያ ተከትሎ መንግስት በትግራይ ክልል በኩል ሰርገው የገቡ የግንቦት ሰባት ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ማለቱ ይታወሳል።

በሰሜን ጎንደር ዞን ስር የሚገኙ ነዋሪዎች በበኩላቸው አካባቢው ውጥረት የነገሰበት መሆኑን በመግለጽ ላይ ሲሆኑ የብሪታኒያ መንግስት የጉዞ እገዳ ስላስተላለፈበት ስፍራ ዝርዝር መርጃን ከመስጠት ተቆጥቧል።