አሜሪካና እንግሊዝ ከመካከለኛ ምስራቅና አፍሪካ ሃገራት የሚጓዙ መንገደኞች ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን ይዘው እንዳይጓዙ እገዳን አስቀመጡ

ኢሳት (መጋቢት 12: 2009)

አሜሪካ ከስምንት የመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ሃገራት ወደ ሃገሪቱ የሚጓዙ መንገደኞች ከማክሰኞ ጀምሮ ላፕቶፕ ኮምፒውተሮችን ጨምሮ ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችንን አብረ ይዘው እንዳይጓዙ እገዳን አስመቀምጠች።

ከሽብር ጥቃት ስጋት ጋር በተገናኘ የተወሰደው ነው የተባለው ይኸው እገዳ በግብፅ፣ ኩዌት፣ ኳታር፣ ሞሮኮ፣ ዮርዳኖስ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ እና በተባበሩት አረብ ኤመሬት የሚገኙ 10 አየር ማረፊያ ጣቢያዎች ላይ ተግባራዊ መደረጉ ታውቋል።

የአሜሪካና የጸጥታ አካላት ከስምንቱ ሃገራት ወደ አሜሪካ የሚጓዙ መንገደኞች ከተንቀሳቃሽ የእጅ ስልካቸው ውጭ ምንም አይነት የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች አብረው ይዘው መጓዝ እንደማችሉ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

የሽብር ጥቃት ለመፈጸም እቅድ ያላቸው ታጣቂዎች የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን እንደሚጠቀሙና ፍንጭ መኖሩን የአሜሪካ የደህንነት ባለስልጣናት ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። ይሁንና ሃላፊዎቹ በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡ ሲሆን፣ ሃገራቱ እገዳውን ተግባራዊ ለማድረግ የ96 ሰዓት ጊዜ ገደብ ተሰጥቷቸዋል።

የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁስ እገዳው በአብዛኛው የሙስሊም ሃገራት ያነጣጠረ ቢሆንም ዕርምጃው ከፕሬዚደንቱ ዶናልድ ትራምፕ የኢሚግሬሽን የጉዞ ፖሊሲ ጋር የተያያዘ አለመሆኑን የአሜሪካ የደህንነት ሃላፊዎች አስታውቋል።

የሆምላንድ ሲኩሪቲ ዲፓትመንት ቃል አቀባይ የሆኑት ጂሊያን ክርስቲንሰን እርምጃው በሃገራት ላይ የነጣጠረ ሳይሆን የስለላ መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ የተወሰደ መሆኑን ለጋዜጠኞች ገልጸዋል። እገዳው ከተጣለባቸው አስሩ አየር ማረፊያ  ጣቢያዎች በየዕለቱ 50 በረራዎች ወደ አሜሪካ እንደሚደረግ ለመረዳት ተችሏል።

አሜሪካ የወሰደችውን ዕርምጃ ተከትሎ የብሪታኒያ መንግስት ተመሳሳይ እገዳን ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑን ቢቢሲ ማክስኞ ምሽት ዘግቧል። ይሁንና የብሪታኒያ የጸጥታ ሃላፊዎች እገዳውን በተመለከተ በቅርቡ ማብራሪያን ይሰጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የዜና አውታሩ አመልክቷል።

የቱርክ መንግስት በበኩሉ አሜሪካ የወሰደችው ዕርምጃ የተሳሳተ ነው በሚል ማስተካከያ እንዲደረግ ጥያቄን ማቅረቡን ቢቢሲ በዘገባው አስነብቧል።

የግብፅ አየር መንገድ በበኩሉ ዕርምጃውን ከአርብ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ባለፈው አመት በሶማሊያ በአንድ የመንገደኞች አውሮፕላን ላይ በላፕቶፕ ኮምፒውተር ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል። የአሜሪካ የደህንነት ባለስልጣናት የሽብር ድርጊትን የሚፈጽሙ አካላት ተመሳሳይ ስልት የመጠቀም እቅድ እንዳላቸው መረጃ መኖሩን ገልጸዋል።