አማራና ኦሮሚያ የሚባሉ ክልሎችን የፈጠረው ኢህአዴግ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 16/2011)አማራና ኦሮሚያ የሚባሉ ክልሎችን የፈጠረው ኢህአዴግ ነው ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

ከማንነት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለማፍረስ የሚደረግ ሙከራ ነው ሲሉም የህወሃት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ ከድምጸ ወያኔ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ እንደገለጹት የወልቃይትና ራያ የማንነት ጥያቄዎች የቀድሞውን የጠቅላይ ግዛት መዋቅር ለመመለስ የሚደርግ እንቅስቃሴ ነው ።

በሌላ በኩል የማንነት ጥያቄን በተመለከተ በአፈጉባዔዋ የተሰጠውን መግለጫ አዛብቶ አቅርቧል በማለት ፌዴሬሽን ምክር ቤት የአማራ መገናኛ ብዙሃንን ወቅሷል።

የአማራ መገናኛ ብዙሃን የመግለጫውን ያልተቆራረጠ ቪዲዮ ሙሉውን ለህዝብ እንደሚለቅ አስታውቋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ ወደ አማራ ክልል ይካለሉ እያሉ አካባቢዎችን እየጠቀሱ የሚጠይቁትን ጂኦግራፊ ምን እንደሆነ ያማያውቁ ናቸው ሲሉ ነው  ለድምጸ ወያኔ በሰጡት ቃለመጠይቅ።

ባህርዳርና ጎንደር ላይ ሆነው ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፣ ራያ አዘቦ የእኛ ነው ብለው የሚጮሁና ሰልፍ የሚወጡ ሰዎች የቀድሞውን ጠቅላይ ግዛት ለመመለስ የሚፈልጉ ናቸው ያሉት አቶ ጌታቸው አማራ ክልልን የፈጠረው ኢህአዴግ፣ አማራ የሚባል ክልል አልነበረም ሲሉ ገልጸዋል።

ወልቃይት፣ ራያም ሆነ ሌላ አካባቢ ወደ አማራ ክልል ይመለስ የሚለው ጥያቄ ህገመንግስቱን የሚያፍርስ እንደሆነም አቶ ጌታቸው በቃለመጠይቁ ላይ አንስተዋል።

‘’የህዝብ ፍላጎትን ግምት ውስጥ ያላስገባ ግዛታችን  የሚል ጥያቄ በታሪክም በህግም አያስኬድም።

በኢትዮጵያ ታሪክ አማራ የሚባል ክልል አልነበረም፣ ኦሮሞ የሚባል አልነበረም፣ ትግራይ የሚባል ክልል አልነበረም።

ምናልባት ትግራይ ለረዥም ግዜ የነበረው ግዛት በተወሰነ መልኩ ተቀራራቢ ነው ማለት ይቻላል።

የትግራይ ክፍለ ሃገር በታሪክም ትግራይ የሚባል የሚታወቅ ክፍል አለ። በታሪክ አማራ የሚባል ክልል ግን አልነበረም፣ አማራ ጠቅላይ ግዛት የሚባልም አልነበረም። በታሪክ አማራ የሚባል አካባቢ አልነበረም።

ኦሮሞ የሚባል ክልል በፊት አልነበረም፣ ኦሮሚያ የሚባል ክልል የኢህአዲግ ህገ መንግስት የፈጠረው ነው። ብለዋል የህወሀቱ አቶ ጌታቸው ረዳ።

አቶ ጌታቸው የህዝብ ፍላጎትን ከግምት ያላስገባ ሲሉ ወልቃይትና ራያዎች በየትኛው ህዝበ ውሳኔ ወደ ትግራይ ክልል እንደተጠቃለሉ የሚገልጽ ማብራሪያ ግን አላቀረቡም።

በትግርኛ ቋንቋ ለድምጸ ወያኔ ቃለመጠይቅ የሰጡት አቶ ጌታቸው ረዳ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በወሎ ክፍለሀገር እንደተፈተኑ የገለጹ ሲሆን እሳቸው ፈተናውን የወሰዱበት አከባቢ አሁን በትግራይ ክልል ውስጥ መጠቃለሉን አለመረዳታቸው አስገራሚ እንደሆነባቸው ነው ቃለመጥይቁን የተከታተሉ ወገኖች የሚገልጹት።

አቶ ጌታቸው በማንነት ዙሪያ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ህገመንግስቱን የሚያፈርስ በመሆኑ እንደህወሀትና ኢህ አዴግ ልናወግዘው ይገባልም ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌደሬሽን ምክር ቤት የአማራ ክልል ብዙሃን መገናኛ በአፈጉባዔዋ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ያቀረበው ዘገባ የተዛባ ነው ሲል ቅሬታውን ማቅረቡ ታወቀ።

ፌደሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤው እንደገለጸው አፈጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ መሃመድ የማንነት ጥያቄን በተመለከተ አጠቃላይ በሆነ መልኩ የሰጡትን ማብራሪያ የአማራ መገናኛ ብዙሃን  ድርጅት ባልደረባ በሚመቸው መልኩ አዛብቶ አቅርቧል ሲል ከሷል።

የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ወዲያውኑ ምላሽ የሰጠ ሲሆን በቀረበው ዘገባ የህግም ሆነ የጋዜጠኝነት ስነምግባር ጥሰት የሌለው ነው ብሏል።