ሐምሌ ፲፩ ( አሥራ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመቀሌ ከተማ ለ3 ቀናት የአማራውና ትግራይን ህዝብ ለማስታረቅ የሚል አጀንዳ የተሰጠው ስብሰባ እክል ገጥሞታል። በብአዴንና በህወሃት የተመለመሉት የአገር ሽማግሌዎች፣ ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንደማያውቁ እየተናገሩ ነው። “በመጀመሪያ ህዝብ ከህዝብ አልተጣላም” የሚሉት ሽማግሌዎች፣ ያልተጣላን ህዝብ እንዴት አድርገው እንደሚያስታርቁ ግራ መጋባታቸውን ይናገራሉ። “ቁርሾው ያለው በህዝቡና በህወሃት መሪዎች መካከል እንጅ በትግራይና በአማራ ህዝብ መካከል አይደለም” የሚሉት ሽማግሌዎች፣ ህወሃት የሚከተለው የዘረኝነት ፖሊሲ የችግሩ መነሻና መድረሻ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ከአማራ የተወከሉ አንዳንድ ሽማግሌዎች “ ያለቀ ነገር ነው የምትናገሩት። የህዝቡ ልብ ከእናንተ ተለይቷል። የሞተ ሰው ተመልሶ አይመጣም፤ አሁን የምተሰሩት የእድሜ ለማራዘም ነው” በማለት በድፍረት መናገራቸው ታውቋል።
የህወሃት ባለስልጣናት ሁለቱ ክልሎች በአጼ ዮሃንስ ዘመንና በደርግ ዘመን አብረው መታገላቸውን በማውሳት እንዲተባበሩና በመካከላቸው ያለውን ጥላቻ እንዲያስወግዱ እየተማጸኑ ነው።
“ጉዳዩ የብሄር ጥል ሳይሆን የፖለቲካ ጥል ነው፤ የፖለቲካን ጥል የብሄር ጥል ያለ አስመስለው የሚያቀርቡ ሰዎች አደገኛ ቁማር እየተጫወቱ ነው” የሚሉት አገር ሽማግሌዎች፣ ብአዴን ቢወገድ የአማራን ህዝብ እንደማይከፋው ሁሉ ህወሃትም ቢወድቅ የትግራይን ህዝብ ሊከፋው አይገባም ይላሉ።
“ህወሃት በአማራው ህዝብ ላይ በትጥቅ ትግልም ወቅት ሆነ ከዚያ በሁዋላ ተደጋጋሚ የጥላቻ ንግግሮችን በመናገሩና ስልጣን ከያዘ በሁዋላም ይህንኑ ጥላቻ ወደ ፖሊሲ ቀይሮ በገሃድ በአማራው ላይ የጭፍጨፋ እርምጃ እየወሰደ በመሆኑ ህዝቡ ህወሃትን ጠልቶታል የሚሉት የአገር ሽማግሌዎች፣ በህዝቡ መካከል ያለው ትስስር ለሺ አመታት የቆየ በመሆኑ፣ ህወሃት በሚወስደው እርምጃ አይበጠስም ሲሉ አስረድተዋል። የትግራይ ተወላጆች አሁንም በአማራ ክልል በሰላም እየኖሩ መሆኑን፣ ህወሃት ስልጣኔን አራዝማለሁ በሚል የተወሰኑ ትግሬዎች ጥቃት እንደደረሰባቸው አድርጎ በዜና እንደሚያራግበው ሽማግሌዎች ገልጸዋል።
ህወሃት የሶማሊ እና የትግራይ ህዝብ አንድነት አይበጠስም በማለት በኦሮሞ ላይ ቅስቀሳ ሲያቀርብ መክረሙን የሚገልጹት ሽማግሌዎች፣ ይህ አካሄዱ አላዋጣው ሲልና በተለይም በሰሜን ጎንደር የሚካሄደው ተቃውሞ ሲበረታበት፣ አማራ እና ትግራይ አንድ ነው በማለት በኦሮሞና በሌሎች የኢትዮጵያ ዜጎች ላይ ሁለቱ ህዝቦች እየተባበሩባቸው እንደሆነ አድርጎ በማቅረብ፣ ህዝብን ከህዝብ የሚከፋፍል ስራ ለመስራት ላይ ታች እያለ ነው በማለት ነቅፈዋል።