ጥቅምት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ለአፍሪካ ዋንጫ ላለፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 5 ሚሊዮን ብር ለመሸለም ቃል የገቡት ሼክ አል አሙዲ ፤ከሸሪኮቻቸው ጋር በመሆን በጨረታ ላሸነፉዋቸው ድርጅቶች የ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ክፍያ ሊፈጽሙ አለመቻላቸው ተዘገበ።
ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ አራት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ለመግዛት የጨረታ አሸናፊነታቸው የተገለጸላቸው የሼክ መሐመድ አል አሙዲና ሸሪኮቻቸው ኩባንያዎች የቅድሚያ ክፍያ ጊዜ ቢራዘምላቸውም፣ በተፈቀደላቸው ቀነ ገደብ ሊከፍሉ አልቻሉም።
ሪፖርተር ምንጮች ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ለአራቱ የልማት ድርጅቶች ግዥ መከፈል የነበረበት የቅድሚያ ክፍያ እስከ መስከረም 30 ቀን 2005 ዓ.ም. እንዲራዘም ተጠይቆ የነበረው በሼክ አል አሙዲ በተፈረመ ደብዳቤ ቢሆንም፣ እስከተጠቀሰው ቀን ድረስ ክፍያው አልተፈጸመም፡፡
የሼህ አል-አሙዲንን የክፍያ ማራዘሚያ ጥያቄ ተቀብሎ የመክፈያ ጊዜው እንዲራዘምላቸው የፈቀደው የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ቦርድ ከዚህ በኋላ ሊወስድ የሚችለው ዕርምጃ ጨረታውን መሰረዝ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡
ሼክ አል አሙዲና ሸሪኮቻቸው በየካቲት 2004 ዓ.ም. በተከናወነ ጨረታ በግዥ እንዲተላለፉላቸው የተወሰኑላቸው የልማት ድርጅቶች፦ የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ አበቦ እርሻ ልማት፣ ቡና ማደራጃና ማከማቻ ፣ጐጀብ እርሻ ልማትና የኢትዮጵያ እምነበረድ ኢንተርፕራይዝ ናቸው፡፡
ሆኖም እስካሁን ለኢትዮጵያ እምነበረድ ኢንተርፕራይዝ ከተከፈለው ክፍያ ውጭ ለቀሪዎቹ የልማት ድርጅቶች የመሸጫ ዋጋ መከፈል የነበረበት ከ 30 እስከ 35 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ አልተከፈለም፡፡
በኤጀንሲው የጨረታ አሠራር መሠረት አንድ ተጫራች አሸናፊነቱ ከተገለጸ በኋላ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ክፍያውን መፈጸም የሚገባው ቢሆንም፣ የሼክ አል አሙዲና የሸሪኮቻቸው ኩባንያዎች ክፍያውን ሳይፈጽሙ ከሰባት ወራት በላይ ዘግይተዋል፡፡
ከሰሪኮቻቸው ጋር በመሆን በጨረታ ላሸነፉባቸው ድርጅቶች ሊከፈል የሚገባውን የቅድሚያ ክፍያ ለሰባት ወራት ያዘገዩት ሼሕ አል አሙዲ ለአፍሪካ ዋንጫ ላለፈው ብሔራዊ ቡድናችን አምስት ሚሊዮን ብር ለመሸለም ቃል ገብተዋል።
ዋልያዎች ከ 31 ዓመት በሁዋላ ላገኙት ታላቅ ድል ከዚህም በላይ ሊደረግላቸው እንደሚገባ እናምናለን ያሉ አስተያዬት ሰጪዎች፤ ግለሰቦች የሚያደርጓቸው የዚህ ዓይነት ሽልማቶች ግን ታላቁን ስህተት መሸፈኛ ሊሆኑ አይገባም ብለዋል።
አንድ ባለሀብት አገርንም ሆነ ህዝብን ሊጠቅም የሚችለው በ አገሪቱ ህግ መሰረት የሚጠበቅበትን እያሟላ ሲሰራና ሲሸልም ነው ያሉት እነዚሁ ወገኖች፤ ህብረተሰቡ ትኩረት በሚያደርግባቸው በኪነ ጥበብ፣ በስፖርትና በሌሎችም ዘርፎች የሚደረጉ ማበረታቻዎች ሁሉ እንደ ግብርና ዕዳ ክፍያ የመሳሰሉ የትላልቅ ስህተት መሸፈኛዎች እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲሉ መክረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በመንግሥት እጅ የሚገኘውን የወርቅ ማምረቻ የሆነውን አዶላ ወርቅን ጨምሮ፣ አሥራ አንድ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በሚቀጥለው ወር ለጨረታ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።
አዶላ ወርቅ በደቡብ ክልል ኦዶላ አካባቢ በወርቅ ማምረት ሥራ ላይ የተሰማራ ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡
መንግስት በፕራይቬታይዜሽን ስም ለግል ባለሀብቶች የሚያስተላልፋቸው የህዝብ ንብረቶች፣ ከፍተኛ የሆነ ሙስና የሚፈጸምባቸው መሆኑ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወቃል።