አልከሄር የኢትዮጵያን ጦር ክፉኛ ወቀሱ

ነሃሴ ፮(ስድስት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሱዳን አብየ ግዛት የሚገኘው የጥምር ኮሚቴ ስብሳቢዎች አንዱ የሆኑት አልከሄር አል ፋቲም አማጺ የሆነውን የሱዳን አብዮታዊ ግንባር በአካባቢው መኖሩ እያወቀ በስፍራው የሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር በዝምታ በማለፉ ክፉኛ ወቅስዋል::

አልከሄር አል ፋቲም ሰሜን ሱዳንን ወክለው የሚገኙ ሲሆን እንደሳቸው ገለጻ አማጺው ሃይል በምስራቅ አብየ ሰፍሮ እንደሚገኝ ገልጸዉ የኢትዮጵያን ጦር ዝምታ ግን የሰላሙን ሂደት እንዳያበላሸው አሳስበዋል:: ቅርብ የሆኑ የተባበሩት መንግስታት ባለስልጣናት እንደገለጹት ከሆነ በሚቀጥሉት ሁለት ወራቶች የአብየ ጉዳይ ባግባቡ ካልተያዘና ሁለቱ አገሮች ወደ ሰላሙ ድርድር ካልተመለሱ አካባቢው ፍጹሙ ወደሆነ ጦርነት ሊገባ ይችላል።

አብየ  ሁለቱ አገሮች የሚከራከሩት ቦታ ሲሆን በደቡብ ሱዳን በኩል ዲንቃ የተባለው የጎሳ አባሎች ባካባቢው የኖሩ ስለሆነ የአካባቢው ግዛት ይገባቸዋል ሲሉ በሰሜን ሱዳን በኩል ደግሞ መሰርያ የተባሉ የጎሳ አባሎች ግዛቱ ይገባቸዋል ስለዚህ እንደነዋሪ መቆጠር አለባቸው የሚል መከራከሪያዎች ይቀርባሉ።

የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ታቦ ምቤኪ በአደራዳሪነት የሚመሩት ፓናል ሁለቱ አገሮች በመሰረተ ሃሳብ ላይ ከተስማሙ በሚመጣው ጥቅምት ወር ህዝበ ውሳኔ እንደሚያ ደርጉ ይጠበቃል ብለዋል::