አልሻባብ በፈጸመው ጥቃት በትንሹ 10 ወታደሮች ተገደሉ

ኢሳት (ሃምሌ 4 ፥ 2008)

የሱማሌ ታጣቂ ሀይል አል-ሸባብ በደቡባዊ ምዕራብ የሞቃዲሾ አካባቢ በአንድ የሶማሊያ የጦር ማዘዣ ጣቢያ ላይ በፈፅመዉ ጥቃት በትንሹ 10 ወታደሮች ተገደሉ።

ታጣቂ ቡድኑ በተሽከርካሪ ላይ በተጠመደዉ ቦንብ አድርሶታል በተባለዉ በዚሁ ጥቃት ቁጥራቸዉ ያልታወቁ ወታደሮች ጉዳት የደረሰባቸዉ ሲሆን ለሰዓታት የቆየ የተክስ ልውውጥ መካሄዱን ሮተርስ የአይን እማኞችን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

ሰኞ ጠዋት በታችኛዉ የሸበሌ ግዛት በሚገኘዉ የላንታ ቡሮ ወታደራዊ አዛዥ ጣቢያ ላይ የተፈፀመዉ ጥቃት ባለፈዉ ወር በአንድ የኢትዬጵያ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ላይ ተፈፅሞ ከነበረዉ ጥቃት በኋላ በአይነቱ የመጀመሪያ እንደሆነ ተነግሯል።

አህመድ ፋሪህ የተባሉ የሱማሊያ ወታደራዊ ባለስልጣን የሱማሊያ ጦር ሰራዊት በወሰደዉ የአፅፋ ምላሽ በትንሹ 12 የታጣቂ ሀይሉ አባላት መግደላቸዉን ለአል-ጂዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ገልፅዋል።

በታጣቂ ሀይሉ ጥቃት የሞቱ ወታደሮች ቁጥርን በተመለከተ  የተለያዩ ቁጥሮች በመነገር ላይ ሲሆን እስክ 30 የሚደርሱ ወታደሮች ስለመሞታቸዉ የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸዉ።

የሱማሊያዉ ታጣቂ ሀይል በወታደራዊ ማዘዥ ጣቢያዉ ላይ በፈፀመዉ ጥቃት ሁለት ወታደራዊ ተሽከርካሪዋችንና አራት ብረት ለበስ ተዋጊ ተሽከርካሪዋችን እንደተወሰደ አል-ጄዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ እማኞችን ዋቢ በማድረግ በዘገባዉ አመልክቷል።

ታጣቂ ሀይሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሶማሊያ በሚገኙ የተለያዩ ግዛቶች እያደረሰ ያለዉ ጥቃት በመጨመር ላይ ሲሆን በሀገሪቱ ተሰማረቶ የሚገኘዉ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሀይል በታጣቂ ሀይሉ ላይ ያስመዘገበዉ ዉጤት እጅጉን አነስተኛ መሆኑ ይነገራል።

በልዕኩ አቅጣጫ ላይ ቅሬታ እንዳደረባቸዉ በቅርቡ የገለፁት የዩጋንዳዉ ፐሬዘዳንት ዩዌር ሙስቬኒ ወደ 6ሺ የሚጠጋ ወታደሮቻቸውን በቀጣዩ ዓመት እንደሚያስወጡ ይፋ ማድረጋቸዉ ይታወሳል። ይሁንና ዩጋንዳ የሰላም አስከባሪ ሀይሏን ለማስወጣት የያዘችው እቅድ ከ10 ዓመት በላይ ሲካሄድ በቆየዉ ሰላም የማስፈኑ ጥረት አሉታዊ ተፅኖን ያሳድራል ተብሎ ተሰግቷል።

ኢትዩጵያን ጨምሮ ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከ20 ሺ በላይ ሰላም አስከባሪዎች በሶማሊያ ተሰማርተዉ ቢገኙም አል-ሸባብ የተሰኘዉ ታጣቂ ሀይል አሁንም ድረስ የፀጥታ ስጋት ሆኖ ይገኛል።