አልሻባብ በኢትዮጵያ ጦር ላይ ጥቃት ሰነዘረ

ኢሳት (ግንቦት 8 ፥ 2008)

በአለም አቀፍ ደረጃ በአሸባሪነት የተፈረጀውና፣ በሶማሊያ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አለው የሚባለው አልሻባብ፣ በሶማሊያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወታደሮችንና የሶማሊያን ሰራዊት ላይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥቃት መሰንዘሩ ተነገረ።

አልሻባብ የወሰደው የጥቃት እርምጃ የተፈጸመው ዛሬ ሰኞ የሂራን የአስተዳደር ማዕከል በሆነችው ባልደዋይን ከተማ አቅራቢያ መሆኑን የሶማሊያ ድረ-ገጾች ከስፍራው እማኞችን በመጥቀስ ዘግበዋል።

በሶማሊያና አለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ለሚዘግብ “ማረግ” ለተሰኘው ድረ-ገፅ የአይን እማኞች እንደተናገሩት፣ የአልሻባብ ተዋጊዎች ከባልደወይን ከተማ በስተምዕራብ በኩል በምትገኘው ሃልጋን በተባለችው አካባቢ ላይ ሰፍሮ በነበረው የሶማልያ ብሄራዊ ሰራዊትና የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ በተለያዩ አቅጣጫዎች ከፍተኛ ጥቃት አድርሰዋል።

የአልሻባብ ተዋጊዎች፣ በኢትዮጵያን ጦርንና በሶማሊያን ስራዊት ላይ በተለያዩ አቅጣጫዎች ባደረሱት ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸው ሙትና ቁስለኛ ወታደሮች ቁጥር በነጻ ምንጮች  እንዳልተረጋገጠ ከስፍራው ዘግበዋል።