ሰኔ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቢቢሲ እንደዘገበው በማእከላዊ ሶማሊያ በተደረገው ጦርነት ታጣቂ ሃይሉ 30 የኢትዮጵያ ወታደሮችን መግደሉን አስታውቋል። ጃሚዮ በተባለ መንደር የሚኖሩ ነዋሪዎች በሁለቱ ሃይሎች መካከል
ከፍተኛ ጦርነት መካሄዱንና ከባድ የጦር መሳሪያዎች ሲተኮሱ መስማታቸውን ተናግረዋል።
አልሸባብ አገኘሁት ያለውን ድል በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተበባለ ነገር የለም። ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ ሆርሲድ ሚዲያ እንደዘገበው ደግሞ የአልሸባብ ተዋጊዎች የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን የጫኑ ወታደሮችን
አድፍጠው በመጠበቅ ጥቃት ፈጽመዋል።
ለ12 ሰአታት ያክል የቆየ በከባድ መሳሪያዎች የታጀበ ጦርነት መካሄዱን ነዋሪዎች ገልጸዋል። አልሸባብ በጥቃቱ 30 ወታደሮችን መግደሉንና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን ማውደሙን ገልጿል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአካባቢው ባለስልጣን የኢትዮጵያ ወታደሮች ተጨማሪ ሃይል እንደሚጣላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
ሞቃዲሾን ከደቡቡ ክፍል ጋር በሚያገናኘው መንገድ ላይ ተደጋጋሚ የደፈጣ ጥቃት ይፈጸማል። ሚያዚያ ላይ 6 የአፍሪካ ህብረት ተዋጊዎች በተመሳሳይ መንገድ ተገድለዋል። የኢትዮጵያ ጦር ወታ ገባ በማለት በሶማሊያ ከ7 አመታት በላይ
አስቆጥሯል። ካለፈው አመት ጀምሮ በአፍሪካ ህብረት ስር ሆኖ በባይዶዋ አካባቢ ጥበቃ እያደረገ ነው።