አልሸባብ 15 የኢትዮጵያ ወታደሮችን መግደሉን አስታወቀ

ጥቅምት ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-አልሸባብ እንደሚለው ሁዱር አቅራቢያ በሚገኝ ሙራ ገቢይ እና ጋርስዌይኒ በተባለ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ባደረሰው ድንገተኛ ጥቃት 25 ወታደሮችን ሲገድል ከእነዚህ ውስጥ 15ቱ የኢትዮጵያ ወታደሮች ናቸው ብሎአል። የክልሉ ባለስልጣን የሆኑት አዳን አብዲ በበኩላቸው በተኩሱ ልውውጥ 50 የአልሸባብ ወታደሮች ተገድለዋል ብለዋል።
በሁለተኛው ቀን ታጣቂ ሚሊሺያው ሞቃዲሹ በሚገኘው ሳሃፊ ሆቴል ላይ ባደረሰው ጥቃት 13 ሰዎች ተገድለዋል። ጥቃቱን የፈጸሙት በሙሉ መገደላቸውን የአፍሪካ ህብረት የሞቃዲሹ ግብረሃይል ቃል አቀባይ ሊዩተናንት ኮሎኔል ፓውል ጂጁንጉ ለአልጀዚራ ገልጸዋል። አልሸባብ በፈጸመው ጥቃት አንድ የፓርላማ አባልን ጨምሮ የፍሪላንስ ጋዜጠኛም ይገኝበታል። የሶማሊያ ወታደራዊ አዛዥ ጄኔራል ጋክማ ዱሊ እና በኢትዮጵያ የሶማሊያ አምባሳደር አብዲሰላም ሃጂ አዳም በጥቃቱ ቆስለዋል።