ኅዳር ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ጦር አሚሶን ቁጥጥር ስር የነበሩ የሶማሊያ ግዛቶች በአልሸባብ ቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው። በደባቡባዊ እና ማእከላዊ ሶማሊያ አካባቢዎች በኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ጦር እጅ የነበሩ አስር ከተሞችን አሸባሪው አልሸባብ ዳግም በቁጥጥሩ ስር ማድረጉን አልጀዚራ ከስፍራው ዘግቧል።
ባለፈው ወር ብቻ የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ጦር የለቀቋቸው አራት ከተሞች ሙሉ ለሙሉ በአልቃይዳ እና አልሸባብ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ውለዋል። የአልሸባብ ወደ ማእከላዊ ሶማሊያ የሚያደርገው ፈጣን ግስጋሴን መጨመር አስመልክቶ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ሕዝባዊ አመጽን ተከትሎ የተፈጠረ የሃይል ሚዛን መዛባት መፈጠሩን አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ወታደሮች ሶማሊያን ለቀው መውጣታቸውን እና ይህን ተከትሎ አብዛሃኛው ከተሞች በአልሸባብ እጅ መግባታቸውን የመንግስት ተወካዮች ማስተባበያ ሰጥተዋል።