ኢሳት (ኅዳር 14 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ የተለያዩ ግዛቶች መውጣቱን ተከትሎ አልሸባብ የተሰኘው ታጣቂ ሃይል ለመጀመሪያ ጊዜ ከአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ጋር ውጊያ ማካሄዱ ተገለጸ።
በታችኛው የሸበሌ ግዛት ተካሄዷል በተባለው በዚሁ አዲስ ግጭት አብዛኞቹ የኬንያ ወታደሮች የሆኑ የሰላም አስከባሪ አባላት ከታጣቂ ሃይሉ ጋር ለሰዓታት የቆየ የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
አልሸባብ የተሰኘው ታጣቂ ሃይል በኬንያ ወታደሮች ቁጥጥር ስር በነበረ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ላይ የከፈተውን ጥቃት ተከትሎ በሁለቱ መካከል ከባድ ውጊያ መካሄዱን የአይን ዕማኞች ለራዲዮ ሸበሌ ገልጸዋል።
በሁለቱም ወገኖች የሞት አደጋ መድረሱ ቢገለጽም፣ የሟቾችን ማንነትና ቁጥር መለየት እንዳልተቻለ የራዲዮ ጣቢያው በዘገባው አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ቁልፍ ከተባሉ ወታደራዊ ይዞታዎች ከለቀቁ በኋላ አልሸባብ በሰላም አስከባሪ ሃይሉ ላይ ጥቃትን ሲሰነዝር ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑም ታውቋል።
ከቀናት በፊት ኬንያ በሶማሊያ የሚገኙ ወታደሮችን በሁለት አመት ውስጥ ጠቅልላ ለማስወጣት የወሰነች ሲሆን፣ ከሶማሊያ ለቀው ለመውጣት የወሰኑ ሃገራት ቁጥር ወደ ሶስት መድረሱን ቢቢሲ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ለአመታት ይዘው ከቆዩት ወታደራዊ ይዞታዎች ለቀው መውጣታቸውን በሰላም አስከባሪ ሃይሉ ላይ ክፍተትን ይፈጥራል ሲሉ የተለያዩ አካላት ሲገልፁ ሰንብተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የሎጂስቲክ ችግር በማጋጠሙ ምክንያት ወታደሮቹ ስትራቴጂካዊ ዕርምጃ ወስደዋል ሲል ሰሞኑን ማረጋገጫ የሰጠ ሲሆን፣ የወታደሮቹን ቁጥር ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ይሁንና አፍሪካ ኮንፊደንሻል የተሰኘና በደህንነት ዙሪያ ዘገባን የሚያቀርብ አንድ የመገኛኛ ብዙሃን ተቋም ከሶማሊያ ለቀው የወጡ ወታደሮች ቁጥር ወደ 12ሺ እንደሚደርስ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ኢትዮጵያውያን ጨምሮ ከዩጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲና ማላዊ የተውጣጡ ወደ 22 ሺ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች በሶማሊያ ተሰማርተው ቢገኙም አልሸባብ የሃገሪቱ የጸጥታ ስጋት ሆኖ መቀጠሉን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ በሰላም አስከባሪ ሃይሉ ስር ካሰማራቻችው ወታደሮች በተጨማሪ ቁጥሩ ያልተገለጸ ጦርን በተናጠል በማሰማራት በሶማሊያ ለሰባት አመት ያህል ቆይታን አድርጋለች።