አልሸባብ በኢትዮ ሶማሌ ድንበር ላይ በምትገኘውን ስልታዊዋ የዋጅድ ከተማ ላይ ጥቃት ፈጸመ

ሚያዝያ ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተሽከርካሪ ላይ የተጠመዱ ከባድ መሳሪያዎችን የጫኑ የአልሸባብ ሚሊሻዎች በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ አዋሳኝ ድንበር ላይ የምትገኘውን ስልታዊዋን የዋጅድ ከተማ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውንም የሶማሊያ ወታደራዊ ባለስልጣናት እሁድ እለት አስታወቁ። በቦቆል ግዛት ውስጥ በደቡባዊ ምእራብ ሶማሊያ ከሞቃዲሾ 305 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የሶማሊያ እና የኢትዮጵያ ወታደራዊ ቤዝ ላይም ጥቃት ፈጽመዋል።
የሶማሊያ ወታደራዊ ባለስልጣኑ ለሸበሌ ራዲዮ ስለሁኔታው ሲያስረዱ ”አልሸባብ ጥቃቱን ባደረሰበት ወቅት ከተማዋ በጨለማ ተዋጠች። ወታደሮችም በአቅራቢያቸው ወደሚገኑ ወታደራዊ ጣቢያዎች ሸሽተዋል።” ብለዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው በከተማዋ የተኩስ ልውውጥ መደረጉን፣ ከፍተኛ የሆነ ፍንዳታዎች መኖራቸውን እና በከተማዋ ወሳኝ የሆኑ የመንግስት ስልታዊ ቦታዎች በሚሊሻዎቹ እጅ መግባታቸውን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል። የአልሸባባ ታጣቂዎች ለሰዓታት ከተማዋን ተቆጣጥረው ከሶማሊያ ወታደራዊ ሃይል ላይ መስሪያዎችን ቀምተው ወደ ነበሩበት ተመልሰዋል። በአሁኑ ወቅት የሶማሊያ መከላከያ ሰራዊት እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዳግም ወደ ከተማዋ መመለሳቸውን ሸበሌ ሚዲያ ኔትዎርክ ዘግቧል።