አልሸባብ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ተሽከርካሪ ላይ የደፈጣ ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 18 ፥ 2009)

የሶማሌው ታጣቂ ሃይል አሸባብ በማዕከላዊ  ሶማሊያ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ተሽከርካሪ ላይ የደፈጣ ጥቃት መፈጸሙን የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን ረቡዕ ዘገቡ።

ይኸው ጥቃት በሂራን ግዛት ስር በምትገኘውና ከበለደወይን ከተማ 40 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የቡርዳር ከተማ መፈጸሙን ጋሮዌ ኦንላይን የተሰኘ የመገናኛ ተቋም የአይን እማኞች ዋቢ በማድረግ በዘገባው አመልክቷል።

በአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል ስር በሚያገለግሉት የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ የተፈጸመውን ይህንኑ ጥቃት ተከትሎ በአካባቢው በሁለቱ ወገኖች መካከል የተኩስ ልወውጥ መካሄዱም ታውቋል።

አልሸባብ በበኩሉ በጥቃቱ ሁለት ወታደሮችን መግደሉና ወታደራዊ ተሽከርካሪ ላይ ውድመት ማድረሱን አስታውቋል።

ይሁንና ታጣቂ ቡድኑ አድርሼዋለሁ ያለው ጉዳት በገለልተኛ አካል ያልተጋገጠ ሲሆን፣ የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ሃይልም እስካሁን ድረስ በጥቃቱ ዙሪያ የሰጠው ምላሽ የለም።

በማዕከላዊ ሶማሊያ የተለያዩ አካባቢዎች የሶማሊያው ታጣቂ ሃይል ተመሳሳይ ጥቃትን በሃገሪቱ ወታደሮች ላይ ሲፈጽም መቆየቱንም ጋሮው ኦንላይን በዘገባው አስፍሯል።

ባለፉት ጥቂት ወራቶች ቁጥራቸው ያልተገለጸ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከማዕከላዊ ሶማሊያ ለቀው መውጣታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በዚሁ አካባቢ ታጣቂ ቡድኑ ይዞታውን አጠናክሮ እንደሚገኝ ይነገራል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከዩጋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ማላዊ፣ ኬንያና ጅቡቲ የተውጣቱ ከ20 ሺ በላይ የሰላም አስከባሪ ሃይሎች በሶማሊያ ተሰማርተው ቢገኙም ታጣቂ ሃይሉ አሁንም ድረስ የሃገሪቱ የጸጥታ ስጋት ሆኖ ቀጥሏል። የአል ሸባብ እንቅስቃሴ ስጋት ያደረባት አሜሪካ በዚሁ ታጣቂ ቡድን ላይ አዲስ ወታደራዊ ዘመቻን ለማካሄድ በቅርቡ ውሳኔ ማስተለለፏ ይታወሳል።

የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል በበኩሉ ከቀጣዩ አመት ጀምሮ የሰላም አስከባሪ ሃይሉን ከሶማሊያ ማስወጣት እንደሚጀምር አስታውቋል።

የሰላም አስከባሪ ሃይሉ ከሃገሪቱ ጠቅልሎ ከመውጣቱ በፊት አሜሪካ ወደ 20ሺ አካባቢ የሚጠጉ የሶማሊያ ወታደሮች ለማሰልጠን እቅድ እንዳላት ገልጻለች።

የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው የሶማሊያው ፕሬዚደንት የአልሸባብ ታጣቂዎች መሳሪያቸውን ካስረከቡ ምህረት እንደሚደረግላቸው ሃሳብን ቢያቀርቡም ታጣቂ ሃይሉ የቀረበለትን ጥሪ ውድቅ አድርጓል።