አልሸባብን ለማስወጣት ተጨማሪ 4 ሺ ወታደሮች ያስፈልጋሉ ተባለ

ኅዳር ፲፬ (አሥራ አራት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በተባበበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ አሚሶም  ስር የተሰማራው  ጦር፣ በአሁኑ ወቅት አልሸባብ ከተቆጣጠራቸው የሶማሊያ ግዛቶች ለማስወጣት ተጨማሪ 4 ሺህ ወታደሮች ማሰማራት እንደሚያስፈልጉት አስታውቋል።

ጁባ ሸለቆ፣ ሂራን፣ በቆል እና አንዳንድ የተወሰኑ የድንበር ከተሞች በአልሸባብ ቁጥጥር ስር ውለዋል። የኅብረቱ ጦር ቃል አቃባይ የሆኑት ኮሎኔል ጆሴፍ ጊበርት እንዳሉት አሁን ካሉ 21 ሽህ 129ወታደሮች በተጨማሪ 4 ሽህ ወታደሮችን ማከል ግድ ነው ። የሶማሊያ ብሔራዊ ምርጫን ተከትሎ በአገሪቷ የሰላምና መረጋጋት ስጋቶች እየጨመሩ ሲሆን ፣ አልሸባብ ሃይሉን በማጎልበት ብዙ አካባቢዎችን በቁጥጥሩ ስር ማዋሉን ኮሎኔሉ ገልፀዋል። ኮሎኔሉ አክለው በአሚሶም ስር ያልታቀፈው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከሶማሊያ መውጣቱን ተከትሎ በማእከላዊ ሶማሊያ ውስጥ የሚገኙ ስድስት ከተሞች በድጋሜ  በአልሸባብ ቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት አልሸባብ የደፈጣ ጥቃቶቹን አጠናክሮ ቀጥሏል። ብዙ ጊዜ ካባከንን እና ተጫማሪ ወታደሮችን ካላሰማራን ሁኔታዎቹ ይበልጥ አስጊ ይሆናሉ ሲሉም ኮሎኔል ጆሴፍ አስጠንቅቀዋል።

ለሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ሃይል የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርገው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ድጋፍ ሰጪ ክፍል፣ለ4ሺህ ወታደሮች የሚሆን ገንዘብ ለመመደብ ፍቃደኝነቱን አላሳየም። የድርጅቱ ረዳት ጸሃፊ የሆኑት ሁበርት ፕሪስ የገንዘብ ምንጭ ማፈላለግ ግድ እንደሚልና ተጨማሪ ወታደሮችን ለማሰማራት ውይይት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

“በአሁኑ ወቅት ገንዘቡን አግኝተናል ፣ ነገርግን ተጨማሪ ሰራዊት የሚሰማራው አሁን ካሉት አገራት ነው ወይስ ከሌሎች አገራት?” በሚለው ጉዳይ  ውሳኔ ላይ ለመድረስ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ውይይት እናደርግበታለን። በዚህ ጉዳይ  ውሳኔ ላይ ለመድረስ ከተለያዩ አገራት የተለያዩ አስተያየቶች እየቀረቡ ነው ሲሉ ባለስልጣኑ ተናግረዋል።

ቡሩንዲ እና ኬኒያ ጦራቸውን ከሶማሊያ ለማስወጣት እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል። ሁለቱም አገራት የደመወዝ መዘግየትና የካሳ ክፍያ ማነስን በምክንያትነት አቅርበዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እርዳታ ለማድረግ ፍቃደኛ አለሆኑን በምክንያትነት በማቅረብ በአሚሶም ስር ያልታቀፉ 2 ሺ ወታደሮችን በቅርቡ ከሶማሊያ ማስወጣቱን ኦል አፍሪካ ዘግቧል።