ኢሳት (ግንቦት 10 ፥ 2009)
አለም አቀፍ የፕሬስ ተቋም የአመቱ የፕሬስ ነጻነት ጀግና ሽልማቱን በዛሬው ዕለት ለጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሰጠ። ሽልማቱን ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ ጀርመን ሃምቡርግ ከተማ ተገኝቶ ተቀብሏል።
አለም አቀፉ የፕሬስ ኢንስቲቲዩት 69ኛው የፕሬስ ነጻነት ጀግና ሽልማት በጀርመን ሃምቡርግ ከተማ በሰጠበት ወቅት፣ ኮፐንሃገን ዴንማርክ የሚገኘው ኢንተርናሽናል ሚዲያ ሪፖርት ተቋም ተባባሪ መሆኑም ተመልክቷል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለፉት 2ሺ ቀናት እኤኣ ከ ሴፕቴምበር 14 ፥ 2011 ጀምሮ በወህኒ ቤት እንደሚገኝ፣ በስነስርዓቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ለፕሬስ ነጻነት ትልቅ አስተዋጽዖ ያደረገና ዋጋ የከፈለ መሆኑም ተወስቷል።
በአውሮፓ ነዋሪ የሆነው የአዲስ ነገር ጋዜጠኛ ማኔጂንግ ኤዲተር የነበረው ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ እስክድርን ወክሎ ሽልማቱን ተቀብሏል። ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል ከጉዞ ሰነድ ጋር በተያያዘ ሽልማቱን መቀበል አልቻለችም።