አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተወካዮች የጋዜጠኝነት ስራቸውን በነጻነት እንዳያከናውኑ በኢትዮጵያ መንግስት ጫና እንደሚደረግባቸው ተገለጸ

ኢሳት (የካቲት 28 ፥ 2008)

መቀመጫቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተወካዮች የጋዜጠኝነት ስራቸውን በነጻነት እንዳያከናውኑ በመንግስት ጫና እየተደረገባቸው መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የውጭ ጋዜጠኞች ማህበር ሰኞ ገለጠ።

ከቀናት በፊት ሁለት የማህበሩ ጋዜጠኞች ለ24 ሰዓት በጸጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታወቀው ማህበሩ በመገናኛ ብዙሃን ላይ እይደረሰ ያለው ወከባ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንም አስታውቋል።

ከአስተርጓሚያቸውንጋር በአፋር ክልል አዋሽ ከተማ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት ሁለቱ አለም አቀፍ ጋዜጠኞች የእጅ ስልካቸውና መታወቂያ ወረቀታቸው በጸጥታ ሃይሎች እንደተወሰደባቸውም ማህበሩ ገልጿል።

በሃገሪቱ ተከስቶ ያለውን የድርቅ አደጋና በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለውን ተቃውሞ የጋዜጠኝነት ሙያ በሚጠይቀው መልኩ ለመዘገብ አለመቻሉንም የጋዜጠኞቹ ማህበር ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በማህበሩ ያልታቀፉ የሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች እና አስተርጓሚዎች እንዲሁም ሌሎች ድጋፍ ሰጪ አካላት ላይ በሚደርሰው መዋከብም ማህበሩ አሳስቦት እንደሚገኝ ገልጿል።

በኢትዮጵያ በነበረው አምስት አመት ቆይታ ለበርካታ ጊዜያት መታሰርን ያወሳው የብሉምበርግ ወኪል ጋዜጠኛ ዊሊያም ዴቪድሰን በሃገሪቱ የሚከሰቱ አበይት ጉዳዮችን ለመሸፋፈን የሚደረገው ጥረት አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ይፋ አድርጓል።

በሃገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ተሰማርተው የሚገኙ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ጋዜጠኞች ለስራ በሚንቀሳቀሱ ጊዘ ከፍተኛ ቁጥጥርን ኣያደረጉ እንደሚገኝም ማህበሩ አክሎ አስታውቋል።

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ሃይል በበርካታ ከተሞች ተሰማርቶ እንደሚገኝ የተለያዩ አካላት ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

ሂውማን ራይትስ ዎችና ሌሎች አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በመገናኛ ብዙሃን ላይ ያለውን አፈና በኦሮሚያ ክልል እየተፈጸመ ያለን ግድያና ኣስራት በአግባቡ ለማወቅ እንዳላስቻለ መግለጻቸውም ይታወቃል።

በሳምንቱ መገባደጃ በሁለቱ አለም አቀፍ ጋዜጠኞች ላይ የተፈጸመውን ድርጊትም እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የውጭ ጋዜጠኞች ማህበር አክሎ አመልክቷል።

በጉዳዩ ዙሪያ መንግስት እስከ አሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የሌለ ሲሆን በርካታ ጋዜጠኞችም ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ዘገባን ለማድረግ ተቸግረው እንደሚገኙ ከሃገር ቤት የተገኘ አመረጃ አመልክቷ።