(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 25/2010) አለም አቀፉ የፕሬስ ነጻነት ቀን ዛሬ በመላው አለም ተከበረ።
በቅርቡ ከወህኒ የወጣው ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋም የፕሬስ ነጻነት ቀንን ለማክበር በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ግብዣ በኬንያ ናይሮቢ ተገኝቷል።
የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝም እለቱን ምክንያት በማድረግ ባስተላልፉት መልዕክት መንግስታት ለመገናኛ ብዙሃን ደህንነት እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
አይፌክስ የተባለው ሃሳብን በመግለጽ ነጻነት ዙሪያ የሚሰራው ተቋም ዛሬ የተከበረውን የፕሬስ ነጻነት ቀን ምክንያት በማድረግ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ካለፈው አመት ግንቦት ጀምሮ በአንድ አመት ግዜ ውስጥ 46 ጋዜጠኞች ሆን ተብሎ በታቀደ ርምጃ ተገድለዋል።
በአመቱ ውስጥ ለግድያ ምክንያት ሆኖ የተገኘውም ከሙስና ማለትም ከሌብነት ጋር በተያያዘ የወጡ ሪፖርቶች መሆናቸውም ተመልክቷል።
ይህም ሌቦችን ያጋለጡ ጋዜጠኞች ይበልጥ አደጋ ላይ የወደቁበት አመት መሆኑን ከአይፌክስ ሪፖርት መረዳት ተችሏል።
ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ ባለፉት 12 ወራት 46 ጋዜጠኞች ሆን ተብሎ በእቅድ ተገድለዋል።
ከነዚህም ሌላ ሌሎች 9 ጋዜጠኞች በስራቸው ላይ እያሉ ሲሞቱ 33ቱ ደግሞ በግጭት አካባቢዎች ዘገባ በማቅረብ ላይ እያሉ ሕይወታቸው አልፏል።
የአለም አቀፉ የፕሬስ ተቋም አይ ፒ አይ እንዳስታወቀው ደግሞ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1997 ጀምሮ ባለፉት 21 አመታት 1801 ጋዜጠኞች ተገድለዋል።
የታሊባን አገዛዝ መገርሰሱን ተከትሎ በቀውስ ውስጥ የምትገኘው አፍጋኒስታን በሳምንቱ መጀመሪያ በቦምብ ፍንዳታ የተገደሉትን 10 ጋዜጠኞቿን በማሰብ የፕሬስ ነጻነትን ቀን አክብራለች።
በልዩ ልዩ የአለም ክፍሎችም የፕሬስ ነጻነት ቀን በተመሳሳይ ተከብሮ ውሏል።
ሃሳብን በመግለጽ ደረጃ ከአለም 150ኛ ከአፍሪካ 40ኛ መሆኗ በሳምንቱ መጀመሪያ የተገለጸው ኢትዮጵያም የፕሬስ ነጻነትን ቀን ማክበሯ ተዘግቧል።
በኢትዮጵያ ሃሳብን የመግለጽ መብት እንዲታፈን የሚሰሩ፣ ሃሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዳይፈቱ ሲጽፉ የነበሩ ግለሰቦችም በኢትዮጵያ የበአሉ ታዳሚና አሳላፊ ሆነው መገኘታቸውንም መረዳት ተችሏል።
ዛሬ የተከበረውን የፕሬስ ነጻነት ቀን በማስመልከት የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ ሚስተር አንቶኒዮ ጉተሬዝ ባስተላለፉት መልዕክት በአለም ላይ ያሉ መንግስታት ለመገናኛ ብዙሃን ደህንነት ይበልጥ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በኬኒያ ናይሮቢ በተከበረው የፕሬስ ነጻነት ቀን ላይ በእንግድነት የተገኘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ማምሻውን ወደ አዲስ አበባ መመለሱም ተሰምቷል።ነገ አርብ ምሽት ከአዲስ አበባ በመነሳት ቅዳሜ ቀትር ላይ ዋሺንግተን ዲሲ ዳላስ አውሮፕላን ማረፊያ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።
የፕሬስ ነጻነት ቀን በየአመቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 3 እንዲከበር የተወሰነው እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1993 በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ነው።
በየአመቱም በዚህ ቀን ሃሳብን የመግለጽ መብት መሰረታዊ መርሆዎች ተነስተው ይወደሳሉ።
በአለም ዙሪያ የፕሬስ ነጻነት ያለበት ፈተና ይገመገማል፣ለፕሬስ ነጻነት ሲሉ ሕይወታቸውን መስዋዕት ያደረጉ የሚወደሱበት ዕለት መሆኑም ታውቋል።