አለም ቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (ግሎባል አልያንስ) በረሃብ ለተጎዱ ወገኖች 1 ሚሊዮን 67ሺ ብር ሰጠ

ኢሳት (መጋቢት 1 ፥ 2008)

አለም ቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (Global Alliance for the Rights of Ethiopians) በድርቅና ረሃብ ተጠቅተው ህይወታቸው ለሞት አደጋ ለተጋለጡ ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መርጃ የሚሆን አንድ ሚሊዮን ስልሳ ሰባት ሺህ ብር ለአለም-አቀፍ የሰብዓዊ እርዳታ ተቋም (ወርልድ ቪዥን) በዋሽንግተን ዲሲ ጽህፈት ቤት ተገኝቶ አስረከበ።

የትብብሩ ሊቀመንበር አክቲቪስት ታማኝ በየነ እና የስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ዶ/ር አክሎግ ቢራራ ለወርልድ ቢዥን አስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ዳይሬክተር ማርክ ስሚዝና ከፕሮግራም አስተዳደር ሃላፊ ክሪስቲን ባሬዶ ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥተዋል።

የተረጂው ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም አንድ ነፍስ ማዳን ቢቻል ትልቅ አስተዋጽዖ ይሆናል ያለው አክቲቪስት ታማኝ በየነ፣ ይህ ዕርዳታ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አለመሆኑን ተናግሯል። በቀጣይም በተለያዩ አገሮች በኢትዮጵያውያን አለም አቀፍ ትብብር ስር በተቋቋሙ ቻፕተሮች የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ እንደሚሰራ በስብሰባው ተናግረዋል።

ረሃብንና ፖለቲካን ለይተን ማየት ይኖርብናል ያለው አቶ ታማኝ፣ የተለያየ የፖለቲካ እምነትና አስተሳሰብ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ በመሆን በዜጎች ላይ ያንዣበበውን የረሃብ አደጋ መቅረፍ እንደሚገባ አስረድቷል። ወርልድ ቢዥንም ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ ዋስትና የሌላቸውን ዜጎችን በመርዳት በኩል ከ40 አመት በላይ በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሰራ ተናግሯል።

በዚህ ውስጥ የፖለቲካ ቁማር እንዲገባ መፍቀድ የለብን ያለው አቶ ታማኝ፣ ነጻ የሆነ ድርጅት ገንዘቡን ወስዶ ለትክክለኛ አላማ እንደሚያውለው አያጠራጥርም ብሏል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚንቀሳቀሰው ወርልድ ቪዥን ለእንደዚህ አይነት ታላቅ አደራ በመመረጡ እጅግ የተደሰቱ መሆናቸውን ሚስተር ማርክ ስሚዝ በበኩላቸው ተናግረዋል። እርዳታውንም በፍጥነት እንደሚያደርሱ ቃል ገብተዋል።

በወርልድ ቢዥን የፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑትና በቅርቡ ኢትዮጵያን የጎበኙት ክሪስቲን ባሬዶ ወርልድ ቪዥን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች አስቸኳይ ምግብ ለሚፈልጉ 10.2 ሚሊዮን በሚበልጡ ህዝቦች ላይ ያንዣበበውን የሞት አደጋ ለማስቀረት ወርልድ ቢዥን እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። በተጨማሪም 2 ሚሊዮን የሚሆን ቤተሰብም ከብቶቻቸው በመሞታቸው ወይም በመሸጣቸው የወደፊት ህይወታቸውን ለመቀየር ከብቶች ሊተኩላቸው ይገባል ብለዋል።

በውጭ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያ ጸሃፊ አቡነ መልከጸዲቅ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን ከአለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያን መብት ጎን በመቆም ሰብዓዊ ርህራሄ እንዲያሳዩ ተማጽነዋል።

አለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት በ2006 ዓም ኢትዮጵያውያን ከሳውዲ አረቢያ ሲባረሩ 120 ሺ የአሜሪካ ዶላር ለአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) መስጠቱ ይታወሳል። በተመሳሳይ መልኩ በሊቢያ ለታገቱ ኢትዮጵያውያን 10ሺ ዶላር፣ በየመን ለነበሩ 32 ሺ ዶላር፣ በማላዊ በዕስር ለነበሩና ወደሃገራቸው ለሚመለሱ ኢትዮጵያውያን 10ሺ የአሜሪካ ዶላር መስጠቱን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።