ኀዳር ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በእንግሊዝኛ አጭር አጠራሩ ፊዳ የተባለው የአፋር ድርጅት ለጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ በጻፈው ደብዳቤ በአፋር ህዝብ ላይ የዘር ማጽዳት በመፈጸም፣ የራስዎን ዘሮች በቦታው ላይ እያስቀመጡ ነው ሲል ከሷል።
ድርጅቱ እንዳለው የአፋር ተፈጥሮአዊ መኖሪያ በሆነው ድክሂል ፣ አርታ፣ በታጁራ ከተማና በኦቦክ በሚገኙ አፋሮች ላይ የጸታ ሃይሎች እስር ግድያ፣ አፈና አስገድዶ መድፈርና ሌሎችንም ኢ ሰብአዊ ድርጊቶች እየፈጸሙ ነው ።
በአገሪቱ በመካሄድ ላይ ባለው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰትና የዘር ማጽዳት ተጠቂ ከሆኑት መካከል የታጁራ ምክትል ገዢ ሱልጣን ሸሂም አህመድ ሞሃመድ የሚገኙበት ሲሆን ፣ከእርሳቸው ሌላ በሲያሩ ባዱል ጎሃር ባደውል እና ሞሃመድ አህመድ የተባሉ የጎሳ መሪዎችም ተይዘው ታስረዋል። በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች፣ ወጣቶች፣ ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎችም የጅቡቲን መንግስት ከሚቃወመው ፍሩድ ከሚባለው ድርጅት ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል መታሰራቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።
የታጁራ ምክትል ገዢ የአፋር ባህላዊ መሪ ሆነው እያለ መታሰራቸው ህገወጥ ብቻ ሳይሆን መቼውንም ተቀባይነት የሌለውና የጅቡቲን የህልውናዋን መሰረት የሚያነቃንቀው ነው የሚለው ፊዳ፣ ምክትል ገዢውን ጨምሮ የታሰሩት በሙሉ በአስቸኳይ ካልተፈቱ ከዚህ ቀደም በመንግስትና በአርዱፍ መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት አደጋ ውስጥ የሚጥለው ነው ብለዋል።
ከ5 አመት በፊት የታሰሩት ሞሃመድ አህመድ ወይም ጃባ በእስር ቤት ከፍተኛ ስቃይ እንደተፈጸመባቸው የገለጸው አለማቀፍ የአፋር ዲያስፖራ ድርጅት፣ ግለሰቡም ሆነ ሌሎች የአርዱፍ አባላት ቤተሰቦች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቋል፡፡
ድርጅቱ አፋሮች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የኢኮኖሚ ማእቀብ መጣሉንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም መንቀሳቀስ አለመቻላቸውም ገልጿል።
በፈረንጆች አቆጣጠር በ1994 እና በ2002 በመንግስትና በአርዱፍ መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን፣ አሁን ለተፈጠረው ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄ ይፈለግ ብሎአል። በአፋር ተወላጆች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙትም ለፍርድ እንዲቀርቡ ፣ የጅቡቲ መንግስትም በአፋር ህዝብ ላይ የሚያካሂደውን ወታደራዊ ጥቃት እንዲያቆም ለፕሬዚዳንቱ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ገልጿል።