አሁን ያለው ሰራዊት “አኩሪ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሆኖ እንዲቀጥል “ እንፈልጋለን ሲሉ የአርበኞች ግንቦት7 ሊ/መንበር ገለጹ ።

ጥቅምት ፲፭ (አሥራ አምስት ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ለመከላከያ ሰራዊቱ ባቀረቡት ጥሪ ፣ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ከነጻነት ሃይሎች ጋር ለሚቀላቀሉ የሰራዊት አባላት የክብር አቀባበል ይደረግላቸዋል። “ሠራዊቱን የሚቀበሉ የሚያስተናግዱና የሚያቋቁሙ ቡድኖችን በየቦታው ማደራጀታቸውን” ፕ/ር ብርሃኑ ገልጸው፣ “ ሕዝብ በህወሓት አገዛዝ ላይ እንጂ በአንተ በሠራዊቱ አባል ላይ የያዘው ቂም” እንደሌለ ተናግረዋል።

“በኢትዮጵያችን ውስጥ እንዲኖር የምንፈልገው ሠራዊት ታማኝነቱ ለፓርቲ ሳይሆን ለሀገር የሆነ፤ ድንበሯን ከጠላት የሚከላከል፤ በሀገር ፍቅር ስሜት የነደደ፤ ሕዝብ የሚወደውና የሚያከብረው ሠራዊት ነው” ያሉት የግንባሩ ሊ/መንበር፣ “ የህወሓት ወንበዴዎች ከዚህ በፊት እንዳደረጉት ሠራዊቱን የመበተን ዓላማም ሆነ ፍላጎት ያላቸው የነፃነት ኃይሎች የሉም” ብለዋል።

ለወደፊቱ የሚፈጠረውን የመከላከያ ሰራዊት በተመለከተ የድርጅታቸውን አቋም ሲገልጹም “ብልሹ መሪዎቹ ተወግደው መዋቅሩ እንደተጠበቀ፤  ሹመትና የደሞዝ ጭማሪ በችሎታና ባደረገው አስተዋጽኦ ብቻ እንጂ ለአንድ ድርጅት ባለው ድጋፍ ወይም በዘውግ ማንነቱ ያልሆነ፤ ሙያውና ተጋድሎው ሀገሩን ከጠላት መጠበቅና የህዝቡን ደህንነት ማረጋገጥ የሆነ፤ በተልዕኮ ላይ ቢሰዋ ህዝቡ እንደጀግና የሚቀብረው፤ አካለ ስንኩል ቢሆን ህዝቡ በአክብሮት እስከ እድሜ ልኩ የሚጦረው፤ መለዮ ለብሶ በህዝቡ ውስጥ ሲገኝ ወጣቱ እንደሱ ለመሆን የሚመኘው አኩሪ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሆኖ እንዲቀጥል ነው” ይላሉ።

መከላከያ ሰራዊቱ የእስከዛሬው በቅቶት መንገዱን እንዲያስተካከልም የመከሩት ፕሮፌሰሩ ፣ “የባርነት አዋጅ ለማስፈጸም ስንል ከሕዝብ ጋር አንዋጋም ብላችሁ በኅብረት ቆማችሁ ይህንን ጦርነት አስቁማችሁ ሀገሪቱን ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ለመውሰድ ታገሉ፣  ይህንን ካልቻላችሁ ደግሞ የሕዝብን ትግል ተቀላቀሉ።” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።