ኅዳር ፳፫ (ሃያ ሦስት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ በአገሪቱ የኢንትርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ ማድረጉን ተከትሎ የሂሳብ ማሽን (ካሽ ሬጀስትራር) የሚጠቀሙ የመርካቶ ነጋዴዎች ፣ ማሽናቸው ከጥቅም ውጭ በመሆኑ እሱን ለማስተካከል ማሽኖችን ወደ ገዡባቸው ድርጅቶች ሲሄዱ በነፍስ ወከፍ 280 ብር እንደሚጠየቁ ነጋዴዎች ተናግረዋል።
“ ችግሩ የእኛ አይደለም፣ ችግሩ የመንግስትና የቴሌ ነው። እኛ ማሸን ግዙ ተብለን ገዛን፣ ቴሌ ደግሞ ኔትወርክ አቋረጠብን፣ ታዲያ ችግሩ መንግስትና ቴሌ ላይ ሆኖ እያለ ለምን እኛ ማስተካከያ ገንዘብ ክፈሉ እንባላለን?” በማለት አንዳንድ ነጋዴዎች ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ የንግድ ድርጅቶች ግን “እኛ እሱን አናውቅም፣ ቴሌን ወይም መንግስትን ጠይቁ” የሚል ምላሽ በመስጠት ነጋዴዎችን በህገወጥ መንገድ እየበዘበዙ መሆኑን ገልጸዋል።
ነጋዴዎቹ የሂሳብ ማሽኑን ካልተጠቀሙ ደግሞ ከአገር ውስጥ ገቢ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
የሂሳብ ማሽኖችን የሚሸጡት ድርጅቶች ከህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተለይም ከቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ባለቤት አዜብ መስፍን ጋር የጥቅም ግንኙነት እንዳላቸው ቀደም ብሎ መዘገቡ ይታወቃል።