ነገ አዲስ አፈ ጉባኤ ሊመረጥ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 10/2010) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ አዲስ አፈ ጉባኤ ሊመርጥ ነው።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው ነገ አዲስ ካቢኔ አቅርበው በፓርላማ ያጸድቃሉ ተብሏል።

በኦሮሚያም የስልጣን ሹም ሽር ተካሂዶ ዶክተር ነገሬ ሌንጮ ከፌደራል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ተነስተው የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ሆነው ተሹመዋል ። ዶ/ር ነገሪን በመተካት አቶ መለስ አለም እንደሚተኳቸው ለአገዛዙ ቅርበት ያላቸው ሚዲያዎች ዘግበዋል።

የፓርላማ አፈጉባኤ ሆነው ሲሰሩ የቆዩት አቶ አባዱላ ገመዳ ነገ ስልጣን ይለቃሉ።

አቶ አባዱላ ጠቅላይ ሚኒስትሩም አፈ ጉባኤውም ከኦሕዴድ ድርጅት መሆን ስለሌለባቸው ከዚሁ ሐላፊነታቸው እንደሚለቁ ቀድመው አስታውቀው ነበር።

እናም አቶ አባዱላ ባሉት መሰረት ነገ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ አፈ ጉባኤ እንደሚመርጥ ለማወቅ ተችሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም አዱሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ የሚያቀርቧቸውን እጩ አዲስ የካቢኔ አባላትን ሹመት ለፓርላማ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቧቸው ሚኒስትሮች ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ለሹመት የሚላኩ ሰዎችን እንደሚያካትት ተገልጿል። አዲስ ከሚሾሙት ሚኒስትሮች መካከል የኢሀዴግ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሺፈራው ሽጉጤ  የግብርና ሚኒስትር  እንደሚሆኑም በአዲስ ፎርቹን ዘገባ ተመልክቷል።የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ በሌላ ሰው  ይተካሉ ተብሏል።በቅርቡ የሕወሃት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ  አባል ሆነው የተመረጡት ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የሆኑትን የብአዴኑን አቶ ያለው አባተን እንደሚተኩም ተዘግቧል።

በነገው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ የፌደራል አስፈጻሚ አካላትን አደረጃጀት ስልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅንም ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላ ዜና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አዲስ ሹመት መስጠቱ ተዘግቧል።

በዚሁም መሰረት በፌደራል ደረጃ ከነበሩ ባለስልጣናት ሁለት ሚኒስትሮችንና አንድ የኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚን የክልሉ ቢሮ ሃላፊዎች አድርጎ ሾሟል።

የኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትሩ ዶክተር ነገሬ ሌንጮም በተመሳሳይ የስልጣን ዘርፍ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ሆነዋል።

ዶ/ር ነገሪን በመተካት የሕወሃት አባል እና የውጭ ጉዳይ ቃል አቅባይ የሆኑት አቶ መለስ አለም እንደሚሾሙ አዲስ ፎርቹን ቅርበት ያላቸውን ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል።

በአንዳንድ ሪፖርቶች  የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ዶ/ር ነገሪ ሌንጮን እንደሚተኩ ሲገለጽ  ነበር።

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ግርማ አመንቴ ደግሞ የኦሮሚያ የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ሃላፊ ሆነው ተሹመዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ሲሳይ ገመቹ ደግሞ የኦሮሚያ ኢንደስትሪያል ልማት ኤጀንሲ ሃላፊ ሆነው መሾማቸውን ለማወቅ ተችሏል።

የኦሮሚያ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ አዲሱ አርጋም የክልሉ የፖለቲካና የገጠር አደረጃጀት ቢሮ ሃላፊ ሆነዋል።

በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች ላይም አዳዲስ ከንቲባዎች ተሹመዋል።