መስከረም ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ መስከረም 26 ቀን 2007 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክርቤቶች መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር በአዲስአበባ ባለፈው ዓመት
22ሺ ያህል የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል የሚል ሪፖርት ማቅረባቸው ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት 22ሺ ያህል ቤቶች ቀደም ሲል ዕጣ ለወጣላቸው ሰዎች መተላለፉን አስተዳደሩ ይፋ ከማድረጉም በላይ አንዳንድ ግለሰቦች የቤቶቹን ቁልፍ ሲረከቡም በዕለቱ ታይተው ነበር፡፡
ነገር ግን 22ሺ የተባሉት ቤቶች ዕድለኞቹ በቴሌቭዥን ከማየታቸው በስተቀር አስካሁን ሊረከቡ እንዳልቻሉ አስረድተዋል፡፡
በየክፍለከተማው ቤቶች ማስተላለፊያ ጽ/ቤት ሄደው ሲጠይቁ «ገና ነው፤ ደውለን እንጠራችሁዋለን» የሚል ተመሳሳይ መልስ እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል፡፡
የቤቶቹ ዕጣ ከደረሳቸው በኃላ በህዳር ወር 2006 ዓ.ም ከንግድ ባንክ ጋር የብድር ውል መፈጸማቸውን፣ በውሉ መሰረት ከአንድ ዓመት እፎይታ በሃሁላ የባንክ ዕዳ መክፈል ግዴታቸው መሆኑንና ቤቶቹን ተረክበው ከኪራይ ቤት
ባልተላቀቁበት ሁኔታ ወደባንክ ዕዳ ክፍያ መሸጋገር እጅግ ከባድና የማይቻል በመሆኑ ሁኔታው እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመ የደረሳቸውን ሐሰተኛ ሪፖርት መሰረት አድርገው 22ሺ ቤቶች ተላልፈዋል ሲሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ መዋሸታቸው የአገዛዙን ይሉኝታ ያጣ ያልተገባ ባህርይ ያሳያል ብለዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ፕሬዚደንት ሙላቱ ተሾመ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር ለተፈጠረው ችግርና መስተጓጎል የኢትዮጵን ሕዝብ በነግግራቸው ይቅርታ መጠየቃቸው አግባብ ቢሆንም ኪሳራው ግን በይቅርታ ብቻ የሚታለፍ
እንዳልሆነ ያነጋገርናቸው የአዲስአበባ ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ኤሌክትሪክ ኃይል ተርፎን ለጎረቤት ሀገር ጭምር ለመሸጥ ችለናል የሚል መንግስት አንዳንዴ በቀን ውስጥ እስከሶስት ጊዜ በተደጋጋሚ ኤሌክትሪክ መቆራረጥ እንደሚያጋጥም የገለጹት አስተያየት ሰጪ፣ አንድ ነዋሪ ይህ ደግሞ
የዜጎችን ገቢ ከመጉዳቱም ባሻገር እንደባንክ፣ ቴሌ ፣አየር መንገድ የመሳሰሉ ከኔትወርክና ኢንትርኔት ጋር የተያያዙ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ስራ የሚፈቱባቸው ጊዜያት እየተበራከቱ እንዲመጣ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ በተለይ እየተስፋፋ ነው በሚባለው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳረፍ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ መካድ አይቻልም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ «ባንክ ቤቶች ሄደህ ተመልከት፡፡ ሰዎች
እንደዳቦ ሰልፍ ቁጭ ብለው ከአሁን አሁን መብራት መጥቶና ኔትወርኩ ተስተካክሎ አገልግሎት እናገኛለን ብለው ተኮልኩለው ሲጠብቁ ታገኛለህ፡፡
አንዳንዴ መብራቱ መጥቶ ኔትወርኩ እምቢ ካለ ቀኑን ሙሉ ተጎልተህ ውለህ ብር ሳታገኝ ወደቤትህ ልትሄድ ትችላለህ፡፡ ይህ ዓይነቱን ቀውስና ኪሳራ ምን ዓይነት ይቅርታ ይተካዋል” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ ፕሬዚደንቱ በንግግራቸው የመብራት መቆራረጥ አንዱ ምክንያት የመልካም አስተዳደር ችግር ነው ማለታቸውን አስታውሶ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ካለ ችግሩን መፍታት፤ ካልተቻለ ለሚችል ኃይል
ስልጣን መልቀቅ እንጂ ዕድሜ ዘላለም ሰበብ እየደረደሩ ለመቀጠል መሞከር ሕዝብን መናቅ ነው ብለዋል፡፡