ኢሳት (ኅዳር 16 ፥ 2009)
ቻይና በጎረቤት ጅቡቲ የባህር ሃይል ወታደራዊ ጣቢያን ለማቋቋም መወሰኗ በህንድ በኩል የደህንነት ስጋት ማሳደሩ ተገለጠ።
የቻይና ወታደራዊ ባለስልጣናት በበኩላቸው ሃገሪቱ በጅቡቲ እየገነባች ያለው ይኸው ወታደራዊ የማዘዣ ጣቢያ ለሰላም ማስከበርና በሰብዓዊ ዕርዳታ ስራዎች እገዛን የሚያደርግ መዕከል እንደሆነ አስታውቃለች።
በተያዘው ሳምንት በጅቡቲ ጉብኝትን ያደረጉ ከፍተኛ የቻይና ወታደራዊ ባለስልጣናት ሃገራቸው ቁልፍ ይዞታ ላይ ትገኛለች በምትባለው ጅቡቲ ወታደራዊ ይዞታን ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ይፋ ማድረጋቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ቻይና በጅቡቲ እየገነባች ያለችው የባህር ሃይል ወታደራዊ ጣቢያ ከሃገሯ ውጭ የመጀመሪያዋ ሲሆን፣ አሜሪካና ፈረንሳይም የቀይ ባህርን የህንድ ውቂያኖስን በምትዋሰንበት ሃገር ተመሳሳይ ይዞታ እንዳላቸው ይታወቃል።
ይሁንና፣ ቻይና በጅቡቲ እየገነባች ያለችው የባህር ሃይል ወታደራዊ ጣቢያ በህንድ በኩል የደህንነት ስጋት ማሳደሩን የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።
ከህንድ በተጨማሪ የቻይና ዕርምጃ በባንግላዴሽ፣ ማይንማር እና በሲሪላንካ ተመሳሳይ የጸጥታ ስጋትን ያሳደረ ሲሆን፣ ቻይና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በእነዚህ ሃገራት ዘንድ ተፅዕኖ ታሳድራለች ተብሎ እንደሚጠበቅ አለም አቀፍ የፖለቲካ ተንታኞች አስታውቀዋል።
የጅቡቲ ጎረቤት ሃገራት የሆኑት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እንዲሁም ሶማሊያ ቻይና እያካሄደች ባለው የወታደራዊ ጣቢያ ግንባታ እስካሁን ድረስ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው ይገኛል።
ፋን ቻንግሎንግ የተባሉ የቻይና ወታደራዊ ባለስልጣን ከቀናት በፊት ከጅቡቲው ፕሬዚደንት ኢስማዔል ኦማር ጉሌ ጋር በተካሄደ ውይይት ወታደራዊ ትብብሩን ለማጠናከር ስምምነት እንደተደረሰ ለሺንሁአ የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።
አሜሪካ፣ ፈረንዳይና ቻይና በጎረቤት ጅቡቲ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያን ከማቋቋም ጎን ለጎን በአካባቢው ወታደራዊ ይዞታቸውን ለማስፋፋትና ለማጠናከር እየወሰዱ ያለው እርምጃ በቀጠናው ወታደራዊ ውጥረትን ሊያመጣ ይችላል ሲሉ ወታደራዊ ባለሙያዎች ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።