ቻይናዎች በኢትዮጵያውያን ላይ የመብት ጥሰት እየፈጸሙ እንደሆነ ታወቀ

ኢሳት ዜና (ጥቅምት 4 ፣ 2008)

በኢትዮጵያ በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያዊያን ሰራተኞች ላይ የሚፈጽመው በደል ከአቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፌደሬሽን ገለጠ።

በኢትዮጵያዊያን ሊሰሩ የሚችሉ ቀላል ስራዎች በውጪ አገር ዜጎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ያስታወቀው ፌደሬሽኑ 20 የሚሆኑ የቻይና ኩባንያዎች ሰራተኞቻቸው በማህበር እንዳይደራጁ ተጽዕኖ አሳድረው እንደሚገኙ አመልክቷል።

በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ በርካታ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያዊያን ዜጎች ላይ የሚፈጽሙት የመብት ጥሰት አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ  መምጣቱን የፌደሬሽኑ ባለስልጣናት የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ለሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች ገልጸዋል።

ችግሩ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎም ፌደሬሽኑ ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት እና ለሌሎች መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች ቢያሳውቅ መፍትሄ ሊገኝ አለመቻሉን የፌደሬሽኑ ፕሬዘዳንት አቶ ዘገየ ሀይለ ስላሴ አስረድተዋል።

የሰራተኛ ማህበር ለማቋቋም በተንቀሳቀሱ ሰራተኞችና አስተባባሪዎች ላይም የቻይና ኩባንያዎች እስከ ማባረር የሚደርሱ እርምጃን እንደሚወስዱና ድርጊቱ ህግን የጣሰ አካሄድ እንደሆነ ሀላፊው አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያዊያን ሊሰሩ የሚችሉ ስራዎች በውጪ ሀገር ሰዎች እንዲሸፈን ማድረጉ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የገለጸው ፌደሬሽኑ፣ ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግስት አካል ትኩረት መስጠት እንዳለበት አሳስቧል።

በቅርቡ ስራውን የጀመረው ቀላል የአዲስ አበባ ባቡር አገልግሎት በርካታ ሰራተኞች የባቡሩን ስራ ተቆጣጥረው እንደሚገኙ ታውቋል።

በቻይናዊያን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ዜጎች ላይ የሚደርሰው በደል ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም ምንም ውጤት ሊመጣ አለመቻሉን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፌደሬሽን አክሎ አስታውቋል።

በሀገሪቱ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ከሚገኙ ቻይናውያን ሰራተኞች በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ አስተናጋጅነት መቅጠሩን መግለጹ የታወሳል ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ60ሺ የሚበልጡ ቻይናዊያን  በተለያዩ ስራዎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።