(ኢሳት ዲሲ–ጥር 7/2010)
የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር በዱከም ሊያደርጉት የነበረው ጉብኝት መሰረዙ ታወቀ።
ለቶኒ ብሌር ጉብኝት መሰረዝ ምክንያቱ በኦሮሚያ ክልል የተነሳው ህዝባዊ እምቢተኝነት መሆኑ ታውቋል።
ህዝባዊ እምቢተኝነቱና የስራ ማቆም አድማው ለሶስተኛ ቀን ተጠናክሮ ቀጥሏል። በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ወደ ተለያዩ አካባቢዎችም መዛመቱ ታውቋል።
ይህንን ተከትሎም የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቶኒ ብሌር በዱከም የነበራቸው ጉብኝት ተሰርዟል።
ቶኒ ቢሊየር ወደ ዱከም የሚያመሩት በቻይና መንግስት ኩባንያ አማካኝነት የተገነባውን የኢንደስትሪ ዞን ለመጎብኘት ነበር።
ከሰኞ የካቲት 5 ጀምሮ በኦሮሚያ አካባቢዎች እየተካሄደ በሚገኘው ተቃውሞና አድማ ሳቢያ መሆኑም ታውቋል፡፡
አዲስ አበባ የሚታተመው ሪፖርተ ጋዜጣ እንደዘገበው የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቶኒ ብሌር አዲስ አበባ የገቡት እሑድ የካቲት 4/2010 ነበር።
በማግሥቱም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተነጋግረው ረፋዱን ወደ ዱከም በማቅናት፣ በቻይና መንግሥት ኩባንያ አማካይነት የተገነባውን የኢንዱስትሪ ዞን ለመጎብኘት እቅድም ይዘው ነበር ብሏል ዘገባው።
እናም በአካባቢዎቹ በተነሳው ተቃውሞና ያንን ተከትሎም መንገዶች በመዘጋታቸውና ህዝብ አደባባይ በመውጣቱ ምክንያት የቶኒ ብሌር ጉብኝት ተሰርዟል።
ቶኒ ብሌር ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ የተለያዩ ተቋማትን በስማቸው ጭምር በማቋቋም በተለይ በአፍሪካ የተለያዩ ሰራዎችን በመስራት ላይ ያገኛሉ።
በተለይም የአፍሪካ ባለስልጣናትን የሚያማክር አፍሪካ ገቨርናንስ ኢኒሺዬቲቭን በመመስረት በማማከር ላይ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል ኢንስቲትዩት ፎር ግሎባል ቼንጅ የሚባል ኩባንያ በመመሥረት በሰው ኃይል አስተዳደር፣ አመራርና በሌሎችም መስኮች ድጋፍ የሚሰጥ አማካሪ ድርጅት አቋቁመዋል።