የካቲት ፪ ( ሁለት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም ባወጣው መመሪያ የኢትዮጵያዊያን ዜግነት የሌላቸው ግለሰቦች በባንኮችና የመድን ሽፋን ሰጪ ኩባንያዎች ውስጥ ያላቸውን የባለቤትነት ድርሻ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም እንዲመልሱ ባዘዘው መሠረት በተለይ አንዳንድ ባንኮች የካፒታል አጣብቂኝ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ የዘርፉ ባለሙያዎች አስጠነቀቁ፡፡
ባለሙያዎቹ እንደሚሉት አንዳንድ ባንኮች በርካታ ቁጥር ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባለአክስዮኖች እንዳሉዋቸው ጠቅሰው እነዚህን አስወጥተው በኢትዮጵያዊያን ለመተካት ረጅም ጊዜ ሊወስድባቸው እንደሚችል፣ በዚህም መካከል ባንኮቹ የካፒታል ቀውስ ውስጥ እንዳይገቡ ሥጋታቸውን እየገለጹ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት 16 የግል ንግድ ባንኮች በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን ሁሉም ባንኮች የብሔራዊ ባንክን መመሪያ ለመፈጸም በመገናኛ ብዙሃን ጥሪ በማቅረብ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ባለአክስዮኖችን ገንዘባቸውን በመመለስ እያሰናበቱ ነው፡፡ በተለቀቁት አክስዮኖች ምትክ ኢትዮጵያንን ለመተካት አንዳንድ ባንኮች ጨረታ ማውጣት ጀምረዋል፡፡ በዚህ ሒደት የአክስዮን ገበያው ተጥለቅልቆ ባንኮቹ በሚፈልጉት ዋጋ ገዥ ላያገኙ ይችላሉ የሚል ሥጋትን ፈጥሮአል፡፡
ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎች እንደሚሉት ብሔራዊ ባንክ መመሪያውን ከማውጣቱ በፊት የባንክ ሥራ አዋጅ ቁጥር 592/2000 የውጪ ሀገር ዜጎች የባንክ ሥራ ውስጥ መሰማራት እንደማይችሉ የደነገገ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በልማት ሥራዎች እንደኢትዮጵያዊያን እንዲሳተፉ የሚፈቅድ አዋጅ ቁጥር 270/2002 መኖሩ ነገሩን አወዛጋቢና ውስብሰብ አድርጎታል፡፡ ይህ አዋጅ የሚከለክለው ለትውልደ ኢትዮጽያዊያን የመምረጥና የመመረጥ መብታቸውን እንዲሁም በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በመሳሰሉት ተቁዋማት ውስጥ መስራትን እንጂ በባንክና ኢንሹራንስ ዘርፎች መሳተፍን አይከለክልም፡፡ በዚህም ምክንያት የብሔራዊ ባንክ መመሪያ አዋጁን የሚጻረር ነው በሚል ተቃውሞ ቢገጥመውም ከመተግበር አላገደውም፡፡
በአንድ በኩል ብሔራዊ ባንክ ባንኮች ካፒታላቸውን ወደ ሁለት ቢሊየን ብር እንዲያሳድጉ መመሪያ የሰጠ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ከፍተኛ የአክስዮን ድርሻ ያላቸውን ትውልደ ኢትዮጵያዊን ከባንኮች ባለቤትነት እንዲሰናበቱ አስገዳጅ መመሪያ ማውጣቱ በተለይ ለባንኮቹ አጣብቂኝ ሆኖባቸዋል፡፡ በተለይ በቅርብ የተቋቋሙ ባንኮች የካፒታል እጥረት ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ባለሙያዎቹ ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአክስዮን ጨረታ ግዥ ማስታወቂዎች በማውጣት አዋሽ ኢንትርናሽናል ባንክ የቀደመ ሲሆን፣ ሌሎች ባንኮች አከታትለው ሊያወጡ ስለሚችሉ የአክስዮን ገበያው መቀዛቀዝን አስከትሎ ሽያጩን በማጓተት ለባንኮቹ የባሰ አጣብቂኝ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል፡፡
ይህን ችግር ለመቅረፍ የባንኮች ጥምረት አንድ መፍትሔ ነው በሚል ባለሙያዎቹ አስተያየታቸውን እየሰጡ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ሁሉም ባንኮች ለዚህ ዓይነቱ ሥራ የተዘጋጁ አለመሆናቸው ሌላው ችግር ነው ተብሎአል፡፡
18ቱም የግልና የመንግሥት ባንኮች በ2008 በጀት ዓመት በጥቅሉ ከታክስ በፊት ከ21.5 ቢሊዮን ብር በላይ አትርፈዋል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ከቀዳሚው በጀት ዓመት ብልጫ ያለው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 13.4 ቢሊዮን ብር በማትረፍ ቀዳሚ ሆኗል፡፡ 16ቱ የግል ባንኮች ትርፍ በጥቅል 6.3 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡