መስከረም ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በስዊዘርላንድ የሚገኘው ቢላል የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ማህበር ከአለም አቀፉ የድምጻችን ይሰማ አስተባባሪ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ባዘጋጀው በዚህ ደማቅ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት የተውጣጡ የኮሙኒቲ ተወካዮች የተገኙበት ሲሆን ይዘውት የመጡትንም የአንድነትና የድጋፍ መልዕክት በሰልፉ ላይ ለተሳተፉ ታዲሚዎች አንብበዋል።
የሰልፉ ዋና አስተባባሪ የሆኑት አቶ ኤልያስ ረሺዴ የዛሬ ሶስት ወር ገደማ ተመሳሳይ ሰልፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው የዛሬው ሰልፍ ካለፈው ትምህርት የተወሰደበትና የተሻለም የህዝብ ብዛት የተገኘበት ነበር ሲሉ ተናግረዋል። ሰልፉ የመብት ፣ የነጻነት ፣ የፍትህ ፣ የዲሞክራሲ ፣ ሰው የመሆን ጥያቄ ነው ሲሉ አውስተው፣ ሃገራችን ኢትዮጵያ የመጻፍ ፣ የመናገር ፣ የመደራጀትም ሆነ በነጻነት ሃሳብን የመግለጽ ሂደቶች በሙሉ የተነፈግንበት የግፍ ምድር ሆናለች ካሉ በሁዋላ ዛሬ ሙስሊሞችን ነጥሎ ኢላማ ያደረገው ይህ ስርዓት ነገ ማን በዚህ ኢላማው ውስጥ እንደሚወድቅ ባናውቅም ያለው ኢ-ፍትሃዊ የሆነው የአመራር አካል ግን በመንገድ ያገኘውን ማንኛውንም አካል በማስወገድ ማለሙን እና ማነጣጠሩን አያቆምም ብለዋል።
በዚህ ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ከክርስትና ዕምነት የመጡ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ከዚህ በፊቱ በዝተው የመገኘታቸው ሚስጥር በኢህአዴግ መንግስት እየተነዛ ያለውን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ያጋለጠና ፍሬ አልባ ያደረገ ከመሆኑም ባሻገር ህዝቦች ለጋራ ችግሮቻቸው የጋራና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የዘርም ሆነ የሃይማኖት ልዩነቶችን ወደ ጎን ትተው በጋራ ፣ በመከባበርና በፍትህ ላይ አንድ ሆኖ ከመስራት ውጭ ሌላ አማራጭ ያለመኖሩን አመላካች ነው ሲሉ የተናገሩት ደግሞ አንጋፋው የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች የሆኑት አቶ መሃመዴ ሃሰና ነበሩ።
እኝህ አንጋፋ ታጋይ የ1966ቱን በግዜው ታላቅ የተባሉትን የኢትዮጵያውያን የሙስሉሞች የመብት ይከበርልን ጥያቄ ሰልፍ በማስተባበርና በግዜው የነበረውን የወጣቶች ክበብ በሊቀመንበርነት መምራታቸው ይታወሳል።
በሰልፉ ሊይ ከተስተጋቡት መፈክሮች መሃከል ድምጻችን ይሰማ ፣ የታሰሩት ኮሚቴዎቻችን ይፈቱ ፣ ሃገር በፍትህ እንጂ በተቀነባበረ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ አትመራም ፣ ሙስሊሙንና ክርስትያኑን ለማጋጨት እየተደረገ ያለው ጥረት ዛሬም ሆነ ወደፊት አይሳካም እና የመሳሰለት ሲሆኑ በብዛት በኦሮምኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የተጻፉ መፈክሮችንም አንግበው ተስተውለዋል። ከዚህ በተጨማሪ የሰልፉን ዓላማና የወደፊት ቀጣይ ትግልን በተመለከተ የሰልፉ አስተባባሪዎች ከገለጹ በሁዋላ ለሚመለከተው የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ቢሮ ደብዲቢያቸውን አስገብተው ወደየመጡበት በሰላም ተመልሰዋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide