መጋቢት ፳፭ (ሃያ አምስት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢሳት ምንጮች ከስፍራው ባደረሱን መረጃ የትናንት ምሽቱ ከፍተኛ ፍንዳታ ከሰሞኑ በከተማዋ ለሦስተኛ ጊዜ የደረሰ ፍንዳታ ነው። በከተማዋ ማዕከል ላይ በሚገኘው በፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ሆቴል ትናንት ምሽት በተፈጸመው የቦምብ ፍንዳታ ሦስት ሰዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ኣስካሁን የሞተ ሰው ስለመኖሩ አልተነገረም።
አካባቢውን ባናወጠው በዚህ ፍንዳታ የፍሎሪዳ ሆቴል መስኮቶች መሰባበራቸውንና በሌሎችም የሆቲሉ ንብረቶች ላይ ጉዳት መድረሱን የዓይን እማኞች ገልጸዋል። የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለስብሰባ በሚያዘወትሩበትና በርካታ ቱሪስቶች በሚዝናኑበት በፍሎሪዳ ሆቴል ፍንዳታው ከተፈጸመ በኋላ አካባቢው በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር መውደቁም ተመልክቷል። ከሰሞኑ ብቻ በጎንደር ከተማ ሦስት የፈንጅ ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን፤ ከጥቃቶቹ ሁለቱ በሆቲሎች ላይ አንድኛው ደግሞ በመዝናኛ ስፍራ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው።
አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች ጥቃቱ እየተፈጸመ ያለው በአገዛዙ በተማረሩ ወገኖች ነው በማለት አስተያዬት ሢሰጡ፤አንዳንዶች ደግሞ ገዥው ፓርቲ ተቀናቃኞቹን ለማፈን ሆነ ብሎ እየፈጸመው ያለው የተቀነባበረ ጥቃት ነው ይላሉ። እስካሁን ይፋዊ በሆነ መንገድ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደ የለም። የገዥው ፓርቲ የጦር መኮንኖች በቅርቡ ጎንደር ከ እጃችን ወጥታለች እንዳሉ መዘገቡ ይታወሳል።