(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 6/2010)
በኢትዮጵያ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ የተቋረጠውን ትምህርት ለማስጀመር አገዛዙ በሀገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች ቢሞክርም እንዳልተሳካለት ተነገረ።
የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የዘር ልዩነት ያመጣውን አገዛዝ በመቃወም ድምጻቸውን በማሰማታቸው በአጋዚ ሃይሎች በመደብደባቸው ግቢውን እየጣሉ ወደ ቤታቸው አምርተዋል።
በአማራ ክልል ባሉ ዩኒቨርስቲዎች የተጎዱ ተማሪዎች ቁጥራቸው በርካታ ነው ተብሏል።
በኢትዮጵያ ካሉ ከ30 በላይ ዩኒቨርስቲዎች ከ15 በላይ በሚሆኑት የመማር ማስተማር ሂደቱ ተቋርጧል።
በተለይም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች የዘር ልዩነት ያመጣውን የሕወሃት አገዛዝ በማውገዝ ትምህርት አቁመዋል።
ተማሪዎቹ ትምህርት በማቆማቸውም የአጋዚ ወታደሮች ወደ ግቢያቸው ዘልቀው በመግባት ከፍተኛ ድብደባ እንደፈጸሙባቸው ነው የተነገረው።
በባህርዳር ዩኒቨርስቲ በዘንዘልማ ግቢ 9 ተማሪዎች፣በይባብ ደግሞ 3 ተማሪዎች በደረሰባቸው ድብደባ ተጎድተው በፈለገ ሕይወት ሆስፒታል እንዲታከሙ ተደርገዋል።
በጎንደር ዩኒቨርስቲ በማራኪና ቴድሮስ ግቢዎች ትምህርት ሲቋረጥ 8 ተማሪዎች ተደብድበው መጎዳታቸው ታውቋል።
በወልድያ፣በደብረታቦርና በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲዎችም ተመሳሳይ ችግር መኖሩ ነው የተገለጸው።
በደብረታቦር ዩኒቨርስቲ 3 ተማሪዎች ሲገደሉ በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ደግሞ በርካቶች መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የአገዛዙ ባለስልጣናት የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶችን ወደ ዩኒቨርስቲ ተቋማት በመላክ ትምህርት ለማስጀመር ያደረጉት ጥረት አልተሳካም ነው የተባለው።
ተማሪዎቹ አገዛዙ ከስልጣን ካልወረደና የዘር መድሎ ስርአቱ ካላበቃ ትምህርት ለመማር የምንችልበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም በማለት ተቃውሟቸውን ቀጥለዋል።
የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ግን ጥያቄያችሁን ለመንግስት እናደርሳለን የእናንተ ችግር የእኛም ችግር ነው በማለት ተማሪዎችን እየደለሉ መሆናቸው ታውቋል።
ተማሪዎቹ ከግቢ የወጡ ተማሪዎች ባልተመለሱበት ሁኔታ፣ ለጥያቄያችን ዱላ መልስ ሆኖ እያለ እንዴት ትምህርት እንጀምራለን በማለት በእምቢተኝነታቸው ቀጥለዋል።