መስከረም ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ትህዴን፣ የቀድሞው የድርጅቱ መሪ ሞላ አስገዶም የተወሰኑ ተከታዮቹን በመያዝ በሱዳን በኩል አድርጎ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ በሰጠው መግለጫ ” የተወሰኑ በትግሉ የቆዩና ግላዊ ጥቅማቸው የተነካባቸው ግለሰቦች ትግሉን ባሻቸው መንገድ ሊጠመዝዙት ስላልቻሉና በአብዛናው ታጋይ በመድረክ ተይዘው መፈናፈና ስላጡ ተስፋ ቆርጠው ከትግሉ ጎራ ሸስተዋል” ብሎአል።
ንቅናቄው ግለሰቦቹን “ለግል ጥቅማቸው ያደሩ” እና ድርጅቱን የማይወክሉ ናቸው በማለት የገለጻቸው ሲሆን፣ ” ትህዴን የቆሸሸውን በመጥረግ ጥንካሬውን ከመቼውም ጊዜ በላይ ያጎለብተዋል እንጅ ትግሉን አያደናቅፈውም” ብሎአል፡
ንቅናቄው በመግለጫው መጨረሻ ” በአገራችን ያለው ጸረ ህዝብ ስርዓት ከስልጣኑ ተወግዶ ህዝባችን የጀመረው የትጥቅ ትግል ግቡን ሳይመታ ለአፍታም ቢሆን ትግሉ ” የማይቆም በመሆኑ ህዝቡ ከትግሉ ጎን ይቁም ብሎአል።
የኢህአዴግ መንግስት ሞላ አስጎደም የኤርትራን መንግስትና አርበኞች ግንቦት7ትን እንዲሰልል የተመደበ መሆኑን የሚገልጽ መግለጫ አውጥቷል።