ቴዲ አፍሮ ኢትዮጵያ የተሰኘውን የሙዚቃ አልበሙን ለማስመረቅ ያዘጋጀው መርሐ ግብር በመጨረሻው ደቂቃ እንዳይካሄድ ታገደ

(ኢሳት ዜና –ነሐሴ 29/2009) ዝነኛው የሙዚቃ ሰው ቴዲ አፍሮ ኢትዮጵያ የተሰኘውን የሙዚቃ አልበሙን ለማስመረቅ ያዘጋጀው መርሐ ግብር በመጨረሻው ደቂቃ መከልከሉ ብዙዎችን ማስቆጣቱ ተሰማ።

ድምጻዊው ቴዲ አፍሮ ቴድሮስ ካሳሁንም ስለተፈጠረው ሁኔታ ማብራሪያ በመስጠት ከሕግ ውጪ የሆነ ድርጊት እንደተፈጸመበት አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በሚለው የሙዚቃ አልበሙ ይበልጥ ተወዳጅነቱ እየጨመረ የመጣውና በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጭምር ሽፋን ያገኘው ቴድሮስ ካሳሁን በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ በአለም አቀፍ የቢልቦርድ ሰንጠረዥ ውስጥ ለቀናት በቀዳሚነት የተቀመጠ መሆኑ ይታወሳል።

ለአዲሱ የኢትዮጵያውያን 2010 አዲስ አመት ዋዜማ በሚሊኒየም አዳራሽ ዝግጅቱን ለማቅረብ ጠይቆ የተከለከለው ቴዲ አፍሮ የሙዚቃ አልበሙን ለማስመረቅ በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ያዘጋጀው ፕሮግራምም በመጨረሻ ሰአት ምክንያቱ ባልተገለጸ ሁኔታ ተከልክሏል።

በመቶዎች ለሚቆጠሩ እንግዶች ጥሪ ከተላለፈና ለሆቴሉ ክፍያ ከተፈጸመ በኋላ የፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ የመንግስት ታጣቂዎች የሙዚቃ መሳሪያዎች ወደ ሆቴሉ እንዳይገቡ በመከልከል ፕሮግራሙን ማሰናከላቸው ታውቋል።

ፖሊሶቹ መሳሪያ እንዳይገባ ከልክሉ መባላቸውን እንጂ የተከለከለበትን ምክንያት እንደማያውቁ ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ የሚለውን የሙዚቃ አልበም ከማስመረቅ ባሻገር ከማር እስከ ጧፍ የሚለውን ዜማ ክሊፕ ለመልቀቅ የተዘጋጀው ይህ ፕሮግራም መስተጓጎሉና መከልከሉ ያስቆጣቸው ወገኖች በማህበራዊ መድረክ የተቃውሞ ድምጻቸውን በማሰማት ላይ ናቸው።

ብርሃኑ ተዘራና አብርሃም ወልዴን ጨምሮ ሌሎች አርቲስቶችም ተቃውሞአቸውን በማሰማት ላይ ናቸው።

ብዙ ቅድመ ዝግጅት የተደረገበት ፕሮግራም በመጨረሻው ሰአት መከልከሉን በተመለከተ ባሰራጨው መግለጫ የሀገሪቱን ሕግ የጣሰ ድርጊት እንደተፈጸመበት አስታውቋል።

ቴዲ በመልእክቱም በተፈጠረው ሁኔታ ጥሪ ለተደረገላችሁ ክቡራን እንግዶቻችንና ለመላው ውድ አድናቂዎቻችን ይህን ይቅርታ ያዘለ መልእክታችንን ስናስተላልፍ መጪው አዲስ አመት የሰላምና የፍቅር ከምንም በላይ ደግሞ መላው የኢትዮጵያ ልጆች በእኩል አይን የሚታዩበት የፍትህ ዘመን እንዲሆን በመመኘት ነው ሲል ተናግሯል።

ያስተሰርያል የሚለውን የሙዚቃ አልበሙን ካወጣበት ከ1997 ወዲህ በኢትዮጵያ የሙዚቃ አልበሙን እንዳያቀርብ ሲከለከል መቆየቱ ይታወሳል።

በመኪና ሰው ገጭተህ ገድለሃል በሚል በተመሰረተበት ክስ ታስሮ የነበረ ሲሆን እርሱ ግን ዛሬም ስለ ንጽህናው እየተናገረ ይገኛል።