ቴክሳስ ግዛት ሂውስተን ከተማ ነዋሪ ኢትዮጵውያን ኢሳትን ለመደገፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ባለፈው ቅዳሜ አካሄዱ

ኢሳት (ታህሳስ 4 ፥ 2009)

ነዋሪነታቸው በዚሁ በአሜሪክ የቴክሳስ ግዛት ሂውስተን ከተማ የሆነ ኢትዮጵውያን ኢሳትን ለመደገፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በሳምንቱ መገባደጃ ቅዳሜ አካሄዱ።

የኢሳትን ስድስተኛ አመት የምስረታ በአል አስመልክቶ በተካሄደው በዚሁ ስነስርዓት ኢሳትን ለመደገፍ ከተካሄደ የጨረታ ገቢ ብቻ ከ20ሺ ዶላር በላይ መገኘቱንና የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ የተሳካ እንደነበር አስተባባሪዎቹ ለኢሳት ገልጸዋል።

የሂውስተን ከተማ የኢሳት ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ሃይሌ ተፈራ በከተማዋ እና ዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ኢሳትን ለመደገፍ አበረታች የሆነ ተነሳሽነት ማሳየታቸውን በስነ-ስርዓቱ ወቅት ተናግረዋል።

በገቢ ማሰባሰቢያ ስነስርዓቱ ኮሜዲያን ክበበው ገዳ ስራዎቹን በማቅረብ ታዳሚዎን ያዝናና ሲሆን፣ የሂውስተን ኢትዮጵያ ወጣቶች ህብረት መድረክን በመምራት አስተዋጽዖ ማበርከታቸውም ታውቋል።

የኢሳትን ስደስተኛ አመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ በተከናወነው በዚሁ ልዩ ዝግጅት “የመንግስት አስተዳደርን” የተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ በዶ/ር ዋለ እንግዳየሁ ቀርቧል። ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ እና ጋዜጠኛ በፍቃዱ ሞረዳ በስነ-ስርዓቱ በመገኘት ኢሳት እያደረገ ባለው አገልግሎት ዙሪያ ከታዳሚዎች ጋር ምክክርን አካሂደዋል። በዚሁ ስነ-ስርዓት ወቅት የሂውስተን ኢትዮጵያ ወጣቶች ህብረትና የከተማዋ ሙስሊም ሴቶች ኢላሚን የተሰኘ ማህበር ለጋዜጠኛ ርዕዮት ሽልማትን አበርክቷል።

የኢሳትን ስድስተኛ አመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ በዚህ በአሜሪካና የተለያዩ ሃገራት በመካሄድ ላይ ያለው ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በቀጣይ በተለያዩ ቦታዎች እንደሚካሄድ የኢሳት አለም አቀፍ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስታውቋል።