(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 20/2010) ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣አቶ አብዱ አሊ ሂጅራን ጨምሮ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን አማካሪ ቦርድ አባል ሆነው ተሾሙ።
ግለሰቦቹ የተመረጡበት መንገድ አነጋጋሪ ሆኗል።
ለአዲስ አበባና ለኦሮሚያ የተዘጋጀው የተቀናጀ ማስተር ፕላን በሕዝባዊ እምቢተኝነት የተሰረዘ መሆኑ የሚታወቅ ነው።
ይህንንም ተከትሎ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ከፍተኛ እልህ የተጋቡና ጥቅማችን ሊቀርብን ይችላል ያሉት የሕወሃት ነባር ባለስልጣናት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በተናጠል እንዲታወጅ አድርገዋል።
ይህ በአዲስ አበባ ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 48/2009 የጸደቀው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንና አፈጻጸሙን የሚቆጣጠረው ኮሚሽን በነዋሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶበታል።
በከተማው ነዋሪ የቀረበው ተቃውሞ ማስተር ፕላኑ ህዝቡ ያልመከረበትና ይሁንታ ያልሰጠው መሆኑን የተገለጸበት ነበር።
የማስተር ፕላኑ አላማም ነባሩን የከተማ ነዋሪ ከቀዬው የማፈናቀልና ከፍተኛ ገንዘብ የመሰብሰብ እንደሆነ በነዋሪዎቹ የቀረበ ነበር።
ለኢሳት አስተያየታቸውን ሰጥተው የነበሩት የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የመሬት አስተዳደር የምህንድስና ዘርፍ አማካሪ ዶክተር ግዛቸው ተፈራ ማስተር ፕላኑ ሕዝባዊ ውይይት እንዳልተካሄደበት ተናግረዋል።
ዶክተር ግዛቸው አክለውም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው መሬት ነጠቃ ልማትን ማዕከል ያላደረገ ከመሆኑም በላይ የሕብረተሰቡን የዲሞግራፊ ስብጥር ለመቀየር በማሰብ የተወጠነ እንደሆነ ገልጸዋል።
በአዲሱ የማስተር ፕላን አማካሪ ቦርድ ውስጥ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣የህግ ባለሙያው አቶ አብዱ አሊ ሒጅራና በንግድ ዘርፍ የተሰማሩት ወይዘሮ ሙሉ ሰለሞን እንዲካተቱ የተደረገበት ምክንያት የሕዝቡን ተቃውሞ ለማዳፈን እንደሆነ እየተገለጸ ነው።
ግለሰቦቹ የተመረጡት ሃሳብ ለማመንጨትም ሆነ ተገቢውን ምክር ለመስጠት ሳይሆን ታዋቂነታቸውን በመጠቀም የመሬት ነጠቃውን ተቀባይነት ለማላበስ እንደሆነ በመነገር ላይ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ድሪባ ኩማ የሕወሃት ጉዳይ አስፈጻሚ፣የከተማው ማዘጋጃ ቤት ሃላፊ አቶ ሀይሌ ፍስሃና የከተማው ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ የሕወሃት ነባር አባላት መሆኑ ይታወቃል።