ታዋቂው የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ታስረው ተለቀቁ

ታኅሣሥስ ፬ (አራት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የተለያዩ አትሌቶችን በማሰልጠን ለውጤት ያበቁት የማራቶን አሰልጣኝ ገመዱ ደደፎ ባለፈው አርብ በወታደራዊ እዙ ( ኮማንድ ፖስት) ተይዘው መታሰራቸውንና ከቀናት በሁዋላ መለቀቃቸው ታወቀ። አሰልጣኙ የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን በኮተቤ ኮሌጅ ተከታትለው ሲወጡ በርካታ ወታደሮች ከበው እንደያዙዋቸው ምንጮች ገልጸዋል።

አሰልጣኙ በምን ምክንያት እንደታሰሩ ባይታወቅም፣ ከአትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ጋር በተያያዘ ሳይሆን እንደማይቀር ግምቶች አሉ። ስለ አሰልጣኙ መታሰር ጥያቄ ያቀረብንላቸው የኢትዮጵያ ኦትሌቲክስ ቡድን መርተው በሪዮ የተገኙት  አሰልጣኝ ሁሴን ሺቦ፣ አሰልጣኝ ገመዱ ታስረው እንደነበርና ትናንት እንደተፈቱ ገልጸዋል። በምን ምክንያት እንደታሰሩ እንደማያውቁ ገልጸዋል።

አሳልጣኝ ገመዱ ደደፎ በሪዮ ኦሎምፒክ ውጤት አለመገኘቱን ተከትሎ ፣ “… ውጤቱን እንደጠበቅነው አላገኘነውም ምክንያቶችን መደርደር አልፈልግም … አትሌቶቻችን ከፍተኛ ፉክክር አድርገዋል…ወርቅ ነገ እናመጣለን …በለንደን አለምአቀፍ ሻምፒዮን እና በቶክዮ ኦሎምፒክ የተሻለ እንሰራለን…” በማለት መናገራቸው ይታወቃል።

በሌላ በኩል አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ሃሳባቸው ተደማጭነት እንዲያገኝ ተጽኖ ከፈጠሩ ሰዎች መካከል አንዱ ሆኖ ተመርጧል። ተቀማጭነቱ አሜሪካ ውስጥ የሆነው ታዋቂው “ኤፍ ፒ” መፅሄት አትሌት ፈይሳ ሌሊሳን እ.ኤ.አ. 2016 ሃሳባቸው በአለም ላይ እንዲታወቅ በድፍረት ከታገሉት 100 ግለሰቦች ውስጥ አንዱ አድርጎ መርጦታል። በሪዮ ኦሎምፒክ በማራቶን ሩጫ የብር ሜዳሊያ አሸናፊው እና በኦሎምፒክ መድረክ የኢትዮጵያዊያንን የመብት ጥሰቶች እጆቹን በማጣመር ለዓለም ሕዝብ በገሃድ ማጋለጡ አትሌት ሌሊሳ ፈይሳን ከተመራጮቹ ውስጥ እንዲካተት እንዳበቃው የመጽሄቱ አዘጋጆች አስታውቀዋል።

አትሌት ፈይሳ ከድሉ በኋላ ”የአገሬን ሕዝብ ብሶት እና ችግር ለዓለም ሕዝብ ሳላሳውቅ በኦሎምፒክ ያገኘሁትን ሜዳሊያ ብቻ ይዤ ወደ አገሬ ብመለስ በሕይወቴ የማይረሳ ፀፀት ውስጥ መውደቄ አይቀርም ነበር” ማለቱ ይታወሳል።

ከአፍሪካ አህጉር ከኢትዮጵያዊው አትሌት ሌሊሳ ፈይሳ በተጨማሪ ዝምባቡያዊው ፓሰተር ኢቫን ማዋሪ ም ተመርጠዋል።