ኢሳት (ጥር 09 ፥ 2008)
ታንዛኒያ በህገ-ወጥ መንገድ ወደሃገሪቱ ገብተዋል ያለቻቸውን 83 ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን በቁጥጥር ስር ማዋሏን ሰኞ አስታወቀች።
የምቤያ ግዛት ፖሊስ ኮማንደር የሆኑት ፒተር ከካምፓ ስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ ወደጎረቤት ማላዊ ለመጓዝ እቅድ እንደነበራቸውና ያለምንም የጉዞ ሰነድ ወደ ታንዛኒያ መግባታቸው ገልጸዋል።
83ቱ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በአንድ የጭነት ተሽከርካሪ ውስጥ በመሆን በጉዞ ላይ እንዳሉ በጸጥታ ሃይሎች ሊያዙ መቻሉን ዘ-ሲቲዝን የተሰኘ የሃገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከልም ሶስቱ በረሃብ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ በመሆኑ ህክምና እንደተደረገላቸው የፖሊስ ኮማንደሩ ለጋዜጣው ተናግረዋል።
እሁድ በቁጥጥር ስር የዋሉት ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በታንዛኒያ የሚገኙ የስደተኛ ቁጥርን ከ300 እንዲበልጥ ያደረገ ሲሆን፣ እነዚሁ ስደተኞች በተለያዩ የታንዛኒያ እስር ቤቶች እንደሚገኙም የታንዛኒያ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ተከትሎ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ወጣት ወደተለያዩ ሃገራት እየተሰደደ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በታንዛኒያ እስር ቤቶች ከሚገኙ ስደተኞች ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችም በጎረቤት ማላዊ እስር ቤቶች መኖራቸውን መዘገባቸን ይታወሳል።
እሁድ በታንዛኒያ የጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር የዋሉት 83 ኢትዮጵያውያን ክስ ይመሰርትባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።