ታንዛኒያ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ልታስገባ መሆኗል አሳወቀች።

መጋቢት ፳፭ (ሃያ አምስት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መዲናይቱን አዲስ አበባን ጨምሮ በርካታ የአኢትዮጵያ ከተሞችና የገጠር አካባቢዎች በኤሌክትሪክ ብርሀን እጦት በተቸገሩበት በአሁኑ ወቅት ታንዛኒያ ከኢትዮጵያ 400 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ልታስገባ መሆኗን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አስታውቀዋል። ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ እንዳሉት ሀገራቸው 57 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ የተፈጥሮ ጋዝ በመጠባበቂያነት ቢኖራትም የኃይል ማመንጫ ግድቦቿ ያሉባቸው አካባቢዎች በድርቁ ምክንያት በመቀነሳቸው ከፍተኛ የኃይል እጥረት አጋጥሟቸዋል። በመሆኑም ከኢትዮጵያ የ400 ሜጋ ዋይት ኤሌክትሪክ ሊገዙ እንደሆነ ማስታወቃቸውን ሮይተርስን በመጥቀስ ስታንዳርድ ዲጂታል ዘግቧል።
ፕሬዚዳንት ማጉፉሊ ሰሞኑን ሀገራቸውን ከጎበኙት ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ከኃይለማርያም ደሳለኝ በዳሬሰላም በሰጡት በዚሁ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከኢትዮጵያ የሚገዛው የአሌክትሪክ ኃይል በከፍተኛ ቮልቴጅ መስመር በኬንያ በኩል አድርጎ ሁለቱን ሀገራት ያገናኛል ብለዋል።
አቶ ኃይለማርያም በበኩላቸው 400 ሜጋዋት ለታንዛንያ ለማቅረብ መስማማታቸውንና እየታዬ የአቅርቦቱ መጠን እንደሚጨምር ተናግረዋል። በዓለማችን በከፍተኛ የኃይል ብቻ ሳይሆን የኤሌክትሪክ ብርሀን እጥረት ከሚሰቃዩ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን፤ ከነዋሪዎቿ አልፎ በአዲስ አበባ በሚደረግ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባን ጨምሮ በታላላቅ ዓለማቀፋዊ ኮንፈረንሶች ላይ በተደጋጋሚ የመብራት መቋረጥ እስከማጋጠም እንደሚደርስ በተደጋጋሚ ተዘግቧል።
የሀገሪቱን የኃይል እጥረት በተወሰነ ደረጃ ሊያቃልል ይችላል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትና በአምስት ዓመትውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የተነገረለት የአባይ ግድብ ግንባታ በስድስተኛ ዓመቱ ገና 50 በመቶ ላይ እንደደረሰ ነው በመንግስት መገናኛ ብዙሀን የተገለጸው።