ታንዛኒያ በሕገ-ወጥ ስደተኞች መጨናነቋን አሳወቀች

ታኀሳስ ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድና ቪዛ ሳይዙ ድንበር ተሻግረው ወደ ታንዛኒያ የሚገቡ የምስራቅ አፍሪካ ስደተኞች ቁጥር እያደር መጨሩንና ሁኔታው ከአገሪቱ አቅም በላይ መሆኑን የታንዛኒያው የአገር ውስጥ ሚንስቴር ቻርለስ ኪታዋንጋ አስታወቁ።
አብዛሃኞቹ ስደተኞች የምስራቅ አፍሪካ ዜጎች ሲሆኑ የኢትዮጵያ፣ሶማሊያና ኤርትራ ዜጎች ቅድሚያውን ይወስዳሉ። በቅርቡ 42 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ዳሬሰላም ውስጥ በሕገወጥ መንገድ ሲገቡ መያዛቸውን ተከትሎ ሚኒስቴሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት ከ10 ሽህ በላይ ሕገወጥ ስደተኞች በታንዛኒያ ካለ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ በመግባታቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
ታንዛኒያ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለሚሻገሩ ስደተኞች መሸጋገሪያ መዳረሻ ናት። የሰብዓዊ መብት ተማጓቾች የታንዛኒያ መንግስት ለስደተኞች ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ ባለ ሁለት አሃዝ እድገት እንዳስመዘገበች ገዢው መንግስት በመገኛኛ ብዙሃን ሌት ከቀን ቢለፍፍም ኢትዮጵያዊያን ግን የማትተካ ሕይወታቸውን ለአደጋ እያጋለጡ መፍለሳቸውን አላቋረጡም።