ታንዛኒያ ሕጻናት የሰውነት ክፍሎቻቸው ተሰርቀው መሞታቸው ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 21/2011)ታንዛኒያ ውስጥ ታግተው የተወሰዱ 10 ሕጻናት የሰውነት ክፍሎቻቸው ተሰርቀው ሞተው መገኘታቸው ተዘገበ።

የአሜሪካው ኬብል ኔትወርክ ሲ ኤን ኤን የታንዛኒያ ምክትል የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩን አነጋግሮ ባጠናቀረው ዘገባ እንዳመለከተው ሕጻናቱ የታገቱት ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ ሲሆን ጥርሶቻቸውን ጨምሮ የሰውነት ክፍሎቻቸው ተወስዶ አስከሬናቸው ተገኝቷል።

ፋይል

የታንዛኒያ ምክትል የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ፋውስቲን ንድጉሊ ድርጊቱን ከጠንቋዮች ጋር አያይዘውታል።

መዳኒት አዋቂ ነን ባዮች ከዚህ ቀደም የህጻናትን የሰውነት ክፍል ያገኘ ሰው ገንዘቡ ይበዛለታል እያሉ ህዝብ ሲያደናግሩ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።

በታህሳስ ወር ተሰውረው ፓሊስ ባደረግው ፍለጋ ከሳምንት በፊት አስከሬናቸው በተገኘው ህጻናት ጉዳይ ላይ ፖሊስ ምርመራ መቀጠሉም ተዘግቧል።

የታንዛኒያ ጤና ጥበቃ ምክትል ሚኒስትሩ ፋውስቲን ንዱጉሊ ከህግ ማስከበሩ ጎን ለጎን ማህበረሰቡን ማስተማርና ከኋላ ቀር አመለካከት ማላቀቅ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

በታንዛኒያና በአንዳንድ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የቆዳ ቀለማቸው በተፈጥሮ ጉድለት የነጣ አልቢኖችን በመግደል የሰውነት ክፍላቸውን መጠቀም ሃይልንም ሃብትንም ያጎናጽፋል የሚል ግድያ የተለመደ ሲሆን ይህ የአሁኑ የህጻናቱ ግድያ ግን በጥቁር ታንዛናውያን ላይ የተፈጸመ መሆኑም ተመልክቷል።

በዓለማችን በተፈጥሮ ጉድለት ቆዳቸውና ጸጉራቸው የሚነጣ ሰዎች ማለትም አልቢኖች በከፍተኛ ቁጥር የሚገኙት በታንዛኒያ እንደሆነም ጥናቶች ያሳያሉ።