ሐምሌ ፲፬ ( አሥራ አራት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ቴያትር ሲነሳ ስማቸው ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚጠራው አንጋፋው የቴያትር ባለሙያ አባተ መኩሪያ ፣ ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ72 ዓመታቸው አረፈ። የቀብሩ ስነስርዓት ሃሙስ በአዲስ አበባ ከተማ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን እንደተፈጸመ መረዳት ተችሏል።
በቲያትር አዘጋጅነት በቲያትርና ስነጥበብ መምህርነት እንዲሁም ቲያትር ቤቶችን በሃላፊነት በመምራት በኪነጥበቡ መስክ ጉልህ አስተዋጽዖ እንደነበረው የሚጠቀሰው አንጋፋው አርቲስት አባተ መኩሪያ “ሃሁ በስድስት ወር” “ቴዎድሮስ” “አሉላ አባ ነጋ” “ኦቴሎ” “ያለአቻ ጋብቻ” ኤዲፐስ ንጉስን” ጨምሮ በርካታ ቲያትሮችን አዘጋጅቷል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቲያትርና ስነጥበባት ዲፓርትመንት በመምህርነት ያገለገለው አባተ መኩሪያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቲያትር ዳይሬክተር እንዲሁም የአዲስ አበባ ባህል ማዕከል ስራ አስኪያጅ በመሆን ማገልገሉንም ከህይወት ታሪኩ መረዳት ተችሏል።
ከ50 አመት በፊት የኢትዮጵያ ቴለቪዥን ሲመሰረት በመዝናኛ ክፍል ውስጥ በሃላፊነት መስራቱ የሚጠቀሰው አንጋፋው አርቲስ አባተ መኩሪያ ህይወቱ ያለፈው ማክሰኞ ሃምሌ 13/ 2008 ዓም ነው።
በ1936 ዓም የተወለደውና በ72 አመቱ ያረፈው አባተ መኩሪያ፣ የቀብሩ ስነስርዓት ሃምሌ 14 ፥ 2008 በአዲስ አበባ መንበረ- ጸባዖት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ከቀኑ 8 ሰዓት እንደተፈጸመ ለማወቅ ተችሏል።
መዲናችን አዲስ አበባ ሕዳር 10 ቀን 1936 ዓ.ም. ከአባታቸው አቶ ስለሺ ማንደፍሮ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ውብነሽ መኩሪያ የተወለዱት አቶ አባተ፣ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነበሩ። የኢሳት ዝግጅት ክፍል ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና አድናቂዎቻቸው መጽናናትን ይመኛል።