ግንቦት ፰(ሥምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢትዮጵያ የሩጫ ታሪክ ሲነሳ ስማቸው በጉልህ ከሚጠሩት የመስኩ ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ወ/መስቀል ኮስትሬ በተወለዱ በስድሳ ስድስት ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ዶክተር ወልደመሰቅል ኮስትሬ በሸዋ ክፍለሃገር ተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ሳሊት እንግዳ ዋሻ በተባለ ቦታ በ1942 ዓ.ም.ተወለዱ። ትምህርታቸውን አዲስ አበባ በመምጣት በደጃዝማች ወንድይራድ ትምህርት ቤት በኮተቤ የመምህራን ኮሌጅ ወደ ባሕር ማዶ በማቅናትም በሃንጋሪ የስፓርት ሳይንስ የተማሩ ሲሆን ድጋሚም ወደ ሃንጋሪ በማቅናት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል።
አሰልጣኝ ዶ/ር ወ/መስቀል ኮስትሬ በአጭር እርቀት ሩጫ ውድድሮች 400,800,1,500 ሜትር አገራቸውን ወክለው የተወዳደሩና በወቅቱ በርቀቱ በአገራችን የክብረወሰን ባለቤትም ነበሩ።
በሙኒክ ኦሎምፒክ አትሌቲክስ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ በመሆን በታላቅ ውድድር ጅማሮዋቸውን ያምዋሹት ዶክተር ወልደመሰቅል ኮስትሬ ለ16 ዓመታት በዘለቀው የዋና አሰልጣኝነት ህይወታቸው 28 የኦሎምፒክ ሜዳልያዎችን በሳቸው መሪነት ያስገኙ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው አጠቃላይ 45 ሜዳልያዎች 62% በመቶውን ድርሻ ይይዛል።
ፊጣ ባይሳ፣ እሸቱ ቱራ፣ ሻለቃ ኃይሌ ገስላሴን፣ ሻለቃ ደራርቱ ቱሉን፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ መሰረት ደፋር፣ ስለሺ ስሕን፣ አሰፋ መዝገቡ፣ ሚሊዮን ወልዴ ወዘተ… የመሰሉ ታላላቅ ሯጮችን ያፈሩ አይዘነጌ የአገር ባለውለታ ነበሩ።
የኢትዮጵያ አጭር ርቀት ሯጭ፣ የእግርኳስ ተጫዋችና የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ዋና አሰልጣኝ፣ የብሔራዊ አትሌቲክስ የአጭር፣ የመሃከለኛና የረዥም ርቀት ውድድሮች አሰልጣኝ የነበሩትና የአገራችን የሩጫ ታሪክ ሲነሳ በቀዳሚነት ስማቸው የሚጠራው ሁለገቡ ባለሙያ አይተኬው የምንጊዜውም ታላቅ ኢትዮጵያዊ የስፓርት ባለሟል ላይመለሱ አሸልበዋል። ስራቸው ግን ለዘላለም በክብር ሲዘከር ይኖራል።
ዶ/ር ወልደመስቀል የአንድ ወንድ ልጅ አባት ሲሆኑ የቀብር ስነስርዓታቸው በነገው እለት ከቀኑ በ8 ሰዓት ላይ በቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ወዳጅ ዘመዶቻቸውና የስፓርት አፍቃሪያን በተገኙበት ይፈጸማል።
የኢሳት ዝግጅት ክፍል ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው የስፓርት አፍቃሪያን መጽናናትን ይመኛል