ኢሳት (ኅዳር 16 ፥ 2009)
ቱርክ ለአውሮፓ ህብረት አባልነት ለመደራደር የተገባላት ቃል ተግባራዊ አለመደረጉን ተከትሎ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ስደተኞችን ወደ አውሮፓ እንዲገቡ ልታደርግ እንደምትችል አሳስባለች።
ባለፈው አመት የሶሪያ ስደተኞች ቱርክን በመጠቀም ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት ሲገቡ የነበረ ሲሆን፣ ህብረቱ ቱርክ ሰደተኞቹን በሃገሩ እንድታቆይ የጥቅማ-ጥቅም ቃል ገብቶ እንደነበር ይታወሳል።
ቱርክ የሃገሩ ዜጎች ያለ ቪዛ ወደ አውሮፓ እንዲገቡና ሃገሪቱ የአውሮፓ ህብረት አባል እንድትሆነ ቃል ከተገባላት መካከል ይገኙበታል።
ይሁንና የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ቱርክ የህብረቱ አባል እንድትሆን በቀረበ የውይይት ሰነድ ላይ ጉዳዩ እንዲዘገይ ውሳኔን እንዳስተላለፉ ቢቢሲ ዘግቧል።
በድርጊቱ ቅሬታ ያደረባቸው የቱርኩ ፕሬዚደንት ታይፕ ኤርዶጋን ሃገራቸው በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የሶሪያና የሌሎች ሃገራት ስደተኞችን ወደ አውሮፓ እንዲገቡ ልታደርግ እንደምትችል አሳስበዋል።
“የገባችሁትን ቃል የማትጠብቁ ከሆነ ድንበራችንን ክፍት እንደምናደርግ መግለጽ እንወዳለን” ሲሉ ፕሬዚደንት ኤርዶጋን ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ይሁንና በርካታ የአውሮፓ አባል ሃገራት ቱርክ እያቀረበች ያለው የማስፈራሪያ በጎ ጎን አይኖረውም ሲሉ ምላሽን የሰጡ ሲሆን፣ ቱርክ በህብረቱ አቋም ቅሬታ እንዳደረባት ገልጻለች።
ሃገሪቱ በአሁኑ ወቅት ሶስት ሚሊዮን የሚሆኑ ስደተኞችን አስጠልላ እንደምትገኝ ታውቋል።
ቱርክ በሃገሯ ያሉ ስደተኞች ወደ አውሮፓ እንዲገቡ የምታደርግ ከሆነ ባለፈው አመት የታየው የስደተኞች ፍልሰት ዳግም ሊቀሰቀስ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
ባለፈው አመት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ስደተኞች በቱርክ በኩል ወደ አውሮፓ መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የስደተኞቹ ሁኔታ በአውሮፓ ህብረት የፖለቲካ መነጋገሪያ ሆኖ ይገኛል።
የአውሮፓ ህብረት ቱርክ ስደተኞቹን በሃገሯ እንድታቆይ የገባውን ቃል ተከትሎ ቁጥር መቀነስ ያሳየ ሲሆን፣ ግሪክ በርካታ ስደተኞች ወደ ቱርክ እንዲመለሱ ማድረጓ የሚታወስ ነው።
በቱርክና በህብረቱ ማካከል የተፈጠረው አዲስ አለመግባባት የስደተኞች ፍልሰት ዳግም እንዲከሰት ያደርጋል ተብሎ ስጋት ማሳደሩንም የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።