(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 24/2010)
በግንቦት 7 ስም በሽብር ወንጀል ተከሰው በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ተከሳሾች ከሳሞራና አባይ ጸሃዬ በላይ ተጠያቂ ናችሁ ሲሉ ዳኞቹን በችሎት ላይ መናገራቸው ታወቀ።
ፍርድ ቤቱም በተከሳሾቹ ላይ እስከ 16 አመታት የሚዘልቅ እስራት የወሰነ ሲሆን ተከሳሾቹም ለሀገራችን ስንል የምንከፍለው ዋጋ ነው ሲሉ በድርጊታቸው እንደሚኮሩ ገልጸዋል።
በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ችሎት የቀረቡትና በእነ ጌታሁን በየነ የክስ መዝገብ የተዘረዘሩት 9 ተከሳሾች በፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።
የቅጣት ውሳኔውም የተከተለው በዚህ ፍርድ ቤት ውሳኔ ስለማናገኝ አንከላከልም ማለታቸውን ተከትሎ ነው።
ፍርድ ቤቱም ከ3 አመት እስከ 16 አመት የሚዘልቅ የእስራት ውሳኔን አሳልፎባቸዋል።
ተከሳሾቹም መንግስታቸው አንድ አመት ስለማይቆይ አያሳስበንም ሲሉ ለፍርድ ቤቱ መመለሳቸው ተመልክቷል።
በእነ ጌታሁን የክስ መዝገብ የተከሰሱትና በግንቦት 7 አባልነት በሽብር ድርጊት ተሳትፋችኋል የሚል ክስ ከቀረበባቸው 14 ተከሳሾች ባለፈው ሕዳር 2010 መጨረሻ እንዲከላከሉ በፍርድ ቤቱ ብይን ተሰጥቷቸው ነበር።
አንደኛውን ተከሳሽ አቶ ጌታሁን በየነንና ዶክተር አስናቀ አባይነህን ጨምሮ ከዚህ ፍርድ ቤት ፍትህ ስለማናገኝ አንከላከልም ያሉት ተከሳሾች ዛሬ ታሕሳስ 24/2010 የእስር ቅጣቱ ውሳኔ ተለልፎባቸዋል።
በዚህም መሰረት አንደኛ ተከሳሽ አቶ ጌታሁን በየነ የ9 አመት እስራት ሲፈረድበት፣2ኛ ተከሳሽ ዶክተር አስናቀ አባይነህና 5ኛ ተከሳሽ አቶ አለማየሁ ንጉሴ እያንዳንዳቸው 16 አመት ከ6 ወር በእስር እንዲቀጡ ተወስኗል።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት በተጨማሪም በ4ኛ ተከሳሽ አቶ ብራዚል እንግዳ ላይ የ15 አመት እስራት መወሰኑ ታውቋል።
በ7ኛ፣በ8ኛ እንዲሁም በ14ኛ ተከሳሾች ያምላክነህ ጌታቸው፣አብዱ ሙሳና ደመላሽ ቦጋለ ላይ ከ3 አመት ከ10 ወር እስከ 5 አመት የሚደርስ ቅጣት አሳልፏል።
ተከሳሾቹም ውሳኔውን ተከትሎ “የታገልንው የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ነው” በማለት በድርጊታቸው እንደማይጸጸቱ ይልቁንም እንደሚኮሩ ገልጸዋል።
“እናንተ ዳኞች ከሳሞራና ከአባይ ጸሃዬ በላይ ትጠየቃላችሁ” በማለትም ዳኞቹን አሳስበዋቸዋል።
“ወያኔ አንድ አመት አይቆይም የጫካ ራዕያችሁም አይሳካም”ያሉት ተከሳሶች “እና የታገልነው ለመቶ ሚሊየን ሕዝብ ነው።ህወሃት ይቀበራል ነጻም እንወጣለን” በማለት በፍርድ ቤቱ ውስጥ ተናግረዋል።
ወደ ታሰሩበት ወደ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት መወሰዳቸውም ታውቋል።