ተከሳሾች በችሎት ውስጥ ተቃውሞ አሰሙ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 30/2010) በቂሊንጦ ቃጠሎ ሰበብ ጥፋተኛ ተብለው ተከላከሉ የተባሉ ተከሳሾች በችሎት ውስጥ ተቃውሞ አሰሙ።

ተከሳሾቹ የፍርድቤቱን ውሳኔ አልቀበልም በማለታቸው ችሎቱ ተረብሾ እንደነበር ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።

በችሎቱ የነበሩ ታዳሚዎችን ፌደራል ፖሊስ ሲበትን እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።

በቂሊንጦ ቃጠሎ ተከሰው ፍርድ ቤት ሲመላለሱ የነበሩት 38ቱ እስረኞች በችሎቱ ጥፋተኛ ሲባሉ ውሳኔውን በመቃወማቸው ረብሻ ተፈጥሮ ነበር።

በቂሊንጦ ቃጠሎ ወቅት በተገደሉት ሰዎች ምክንያት ከተከሰሱትና እንዲከላከሉ ከተወሰነባቸው መካከል 34ኛ ተከሳሽ ፍጹም ጌታቸው የመረረ ተቃውሞ ማሰማቱ ተገልጿል።

“በቃጠሎው የተገደለው አብሮ አደጌ፣የሰፈሬ ልጅ፣ጓደኛዬ ነው።አባቴ የእሱን ሞት ሰምቶ እኔም ያለሁበት መስሎት በልብ ድካም ነው የሞተው”ሲል ምሬቱን ለችሎቱ አሰምቷል።

ከውሳኔው በኋላ ችሎቱ ሲረበሽ የፍርድ ቤቱ ታዳሚዎች ጩህት በመስማታቸው አካባቢው መረበሽ መጀመሩን ያገኘንው መረጃ ያመለክታል።

የፌደራል ፖሊስ ታዳሚዎችን በሃይል ሲበትን እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።ፖሊስ መሳሪያ በማቀባበል በችሎት በተገኙ ሰዎች ላይ በማነጣጠር ሲያስፈራራ እንደነበርም ነው የተነገረው።

በቂሊንጦ ቃጠሎ ሰበብ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤን ጨምሮ የልብ ሃኪሙ ዶክተር ፍቅሩ ማሩ እንደሚገኙበት ይታወቃል።

በፍርድቤቱ ውሳኔ መሰረት የእነ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ክስ ከሽብር ወንጀል ወጥቶ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ እንዲታይ ይደረጋል።

በዚሁም መሰረት መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ፣ወልዴ ሞቱማ፣ አግባው ሰጠኝ፣ፍቅረ ማርያም አስማማው አበበ ኡርጌሳ በእስር ቤት አመጽ በማደራጀትና በመምራት ወንጀል ይከላከሉ ተብለዋል።

ዶክተር ፍቅሩ ማሩም ይከላከሉ ከተባሉት መካከል ይገኙበታል።ይህም ሆኖ ግን ከ39ኙ ተከሳሾች 8ቱ ነጻ ተብለው እንዲለቀቁ ተወስኗል ተብሏል።