ተቃውሞው ዛሬም ቀጥሎ መዋሉ ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 11/2010)

በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ዛሬ ተቃውሞ መካሄዱ ተገለጸ።

በዱከም የቻይና የኢንዱስትሪ ዞን መመስረትን በመቃወም ሰልፍ ተካሄዷል።

መቱ ለሶስተኛ ቀን ተቃውሞ ተደርጎባታል። በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ዛሬ ግጭት መፈጠሩም ታውቋል።

በድሬዳው ዩኒቨርስቲ ዛሬ ግጭት መፈጠሩን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ባለፈው ሰኞ በርካታ ተማሪዎች የተጎዱበት ግጭት ከተከሰተ በኋላ ዩኒቨርስቲው በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበረ ቢሆንም ዛሬም በተማሪዎች ተቃውሞ ተቀስቅሷል።

በኢሉባቡር መቱ ለ3ኛ ቀን በተካሄደ የተቃውሞ ትዕይንት ልብሳቸውን ያወለቁ ወጣቶች አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

በአዲስ አበባ አቅራቢያ ባለችው ዱከም ከተማ የቻይናን የመሬት ወረራ በመቃወም ሰልፍ ተደርጓል።

የቻይና የኢንደስትሪ ፓርክ መመስረት ያስቆጣቸው የዱከም ነዋሪዎች አደባባይ በመውጣት አጠቃላይ የመሬት ቅርምትን ያወገዙ ሲሆን በአስቸኳይ ወረራው ካልቆመ ርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል።

በኢሉባቡር ገቺ ወረዳ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ እንደተስተጓጎለ ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

ተማሪዎች የመከላከያ ሰራዊት ከአካባቢው ካልወጣ አንማርም የሚል ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ አብዛኞቹ በወረዳው የሚገኙ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውም ተገልጿል።

በአርሲ ጎባ ሮቢም በተመሳሳይ ተቃውሞ ተካሂዷል። ሀረርጌ ጭናክሰን ቄሌም ወለጋ ተቃውሞ ከተደረገባቸው አባባቢዎች የሚጠቀሱ ናቸው። በሌላ በኩል የመከላከያ ሰራዊት በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች መግባቱን የቀጠለ ሲሆን በአምቦ መስመር በኦራል ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች የመከላከያ ሰራዊቱ ቅኝት በማድረግ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።